የጤና ሙያን ስለመሰየምና የሙያ ስራ ፈቃድ ስለመስጠት
ማንኛውም ሰው ከባለስልጣኑ የሙያ ስራ ፈቃድ ሳያገኝ በጤና ሙያ መስክ መሰማራትና የጤና አገልግሎት መስጠት አይችልም፡፡ የሙያ ስራ ፈቃድ ለማግኘት መሟላት ስላለባቸው መስፈርቶች ማንኛውም ሰው በጤና ሙያ ለመሰማራትና የሙያ ስራ ፈቃድ ለማግኘት የሚከተሉትን መስፈርቶች ማሟላት አለበት፡፡
1. በትክክል የተሞላ የሙያ ምዝገባና ፈቃድ ጥያቄ ፎርም
2. ከተመረቀበት ኮሌጅ ወይም ዩኒቨሪሲቲ የተሰጠ የተማረውን የትምህርት ዓይነትና ትምህርቱን ስለማጠናቀቁ የሚገልፅ ማስረጃ (ሰረተፊኬት፣ ዲፕሎማ፣ ዲግሪ፣ ትራንስክሪፕት)
3. የሙያ ብቃት ምዘና ያለፈ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሰርተፍኬት (የሙያ ብቃት ምዘና እንዲወስዱ ለተመረጡ የሙያ ዘርፎች)፤
4. ወቅታዊ የሆነ በሙያቸው መመዝገባቸውን የሚያረጋግጥ የሙያ ስራ ፈቃድ (ከዚህ በፊት በሌላ ሀገር እንደ ጤና ባለሙያ ሲሰሩ ለቆዩ ባለሙያዎች)
5. የሙያ ብቃትና ስነ-ምግባር ሁኔታን የሚገልጽ አግባብ ያለው የስራ ልምድ (LETTER OF GOOD STANDING) (ከዚህ በፊት በሌላ ሀገር እንደ ጤና ባለሙያ ሲሰሩ ለቆዩ ባለሙያዎች)
6. እንግሊዝኛ ተናጋሪ ካልሆኑና ስርዓተ ትምህርታቸው በእንግሊዝኛ ከማይሰጥባቸው አገሮች ለሚመጡ የውጭ ሀገር ዜጎች የእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት
7. ሶስት ወር ያላለፈውና ባለሙያው ሙያውን ለማከናወን በሚያስችል የጤና ሁኔታ ላይ እንዳለ የሚያረጋግጥ የህክምና ምስክር ወረቀት፤
8. ስድስት ወር ያላለፈው ሁለት ፓስፖርት መጠን ፎቶግራፍ
9. የአገልግሎት ክፍያ የከፈለበት ደረሰኝ
10. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀፅ (2)፣ (4) እና (5) ስር የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ ከውጭ ሀገር ለሚመጡ የጤና ባለሙያዎች የሚያቀርቡት ማስረጃ ስልጣን በተሰጠው አካል ህጋዊነቱ የተረጋገጠና በእንግሊዘኛ ቋንቋ ካልሆነ ህጋዊ በሆነ አካል ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመ መሆን ይኖርበታል፡፡
የሙያ ስራ ፈቃድ ስለማሳደስ
1. ማንኛውም የጤና ባለሙያ የተሰጠውን የሙያ ፈቃድ በየአምስት ዓመቱ ማሳደስ አለበት፡፡
2. ማንኛውም የጤና ባለሙያ የተሰጠውን የሙያ ስራ ፈቃድ የጊዜ ገደብ ከመጠናቀቁ አንድ ወር በፊት የእድሳት ጥያቄ ማቅረብ አለበት፡፡
3. ለሙያ ፈቃድ እድሳት የሚያመለክት ባለሙያ የሚከተሉትን መስፈርቶች ማሟላት አለበት፡-
በትክክል የተሞላ የማመልከቻ ቅጽ
ከዚህ በፊት የተሰጠ የሙያ ስራ ፈቃድ፤
የሙያ ብቃትና ስነ-ምግባር ሁኔታን የሚገልጽ ከሚሰራበት ተቋም አግባብ ባለው ኃላፊ የተጻፈ የስራ ልምድ፤
በተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ መመሪያ ላይ የተቀመጠውን የተከታታይ የሙያ ማጎልበቻ መውሰዱን የሚያረጋግጥ ማስረጃ፤
ሶስት ወር ያላለፈው ሙያውን ለማከናወን በሚያስችል የጤና ሁኔታ ላይ እንዳለ የሚያረጋግጥ የህክምና ምስክር ወረቀት፤
ስድስት ወር ያላለፈው ሁለት ፓስፖርት መጠን ፎቶግራፍ፤ እና
የአገልግሎት ክፍያ የተከፈለበት ደረሰኝ፡፡
4. ከአንድ ሙያ በላይ ለመስራት የሙያ ስራ ፈቃድ ያገኘ ባለሙያ ለእያንዳንዱ ሙያ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (3) የተቀመጠውን መስፈርት ማሟላት አለበት፡፡
5. ትምህርቱን በውጭ ሀገር ያጠናቀቀ፤ በባለስልጠኑ የሙያ ስራ ፈቃድ የተሰጠውና በሀገር ውስጥ የሚሰራ በበቂ መጠን በገበያ ላይ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ የጤና ባለሙያ የሙያ ስራ ፈቃዱን የሚያሳድሰው በሚሰራበት ክልል በሚገኝ የክልል ጤና ተቆጣጣሪ አካል ይሆናል፡፡
6. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) እና (2) ስር በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ የሙያ ስራ ፈቃዱ ያላሳደሰ ባለሙያ ከአምስተኛው ዓመት መጨረሻ ቀን ቀጥሎ ባለው ቀን ጀምሮ ከእድሳት የአገልግሎት ክፍያው በተጨማሪ በየወሩ ለእድሳት የተቀመጠውን የክፍያ መጠን ቅጣት በመክፈል ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ማሳደስ ይችላል፡፡
7. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀፅ (1)፣ (2) እና (5)መሠረት ሳያሳድስ የቀረ ባለሙያ ያለ ሙያ ስራ ፈቃድ እንደሰራ ተቆጥሮ ባለስልጣኑ አስተዳደራዊ እርምጃ ይወስዳል፡፡
ለመረጃ
ስልክ፦ +25146220
ኢሜይል፦ pqca@snnprhb.gov.et