በወጣቶችና በአፍላ ወጣቶች የስነተዋልዶ ጤናና የወጣት ባለትዳሮችን የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማሻሻል የሚያግዝ አዲስ ፕሮጀክት ትዉዉቅ ተደርጎአል

የወደፊት ህይወታቸዉን ማግኘት (Owning Their Future) ፕሮጀክት በማሪስቶፕስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ እና በአለም አቀፍ የህዝብ አገልግሎት (PSI) ጥምረት የተመሰረተ ፕሮጀክት ሲሆን በቀጣይ አራት አመት ወጣት የገጠር ባለትዳሮች በኢኮኖሚና በስነልቦና ዝግጁ ከመሆናቸዉ በፊት ልጅ መዉለድ የሚያስከትለዉን ዉስብስብ ጫና ተገንዝበዉ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆን በወጣትነት እድሜ ላይ ከሚከሰት ህመምና ሞት ራሳቸዉን የሚጠብቁበትን ሁኔታ የሚያመቻች ፕሮግራም መሆኑን በዛሬዉ ዕለት በተደረገዉ የፕሮጀክት ማስተዋወቂያ መድረክ ላይ ተጠቁሟል፡፡

በዚሁ ወቅት የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መ ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊና የፕሮግራሞች ዘርፍ አስተባባሪ የሆኑት አቶ መና መኩሪያ በመልዕክታቸዉ አፍላ ወጣትነት ከጉርምስና ወደ አዋቂነት የሚደረግ የሽግግር ወቅት እና አካላዊና ስነልቦናዊ እድገት የሚከሰትበት የእድሜ ክልል መሆኑን ጠቁመዉ
የወጣትነት ባህሪን ታሳቢ ያደረገ የጤና ፕሮግራም ተደራሽ ለማድረግ በመንግስት እየተሰሩ ካሉ ስራዎች በተጨማሪ በስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት ላይ የረጅም ጊዜ ልምድ ባላቸዉ አጋር ድርጅቶች መታገዝ ዉጤታማነቱን የሚያፋጥን በመሆኑ የወደፊት ህይወታቸዉን ማግኘት (Owning Their Future) ፕሮጀክት በክልሉ በ5 ዞኖችና በ15 ወረዳዎች ከመንግስት መዋቅሩ ጋር ተቀናጅቶ የሚሰራ ስራ በመሆኑ በክልል፣በዞንና በወረዳ ደረጃ ለወጣቶች፣ ለአፍላ ወጣቶችና ለገጠር ወጣት ባለትዳሮች ልዩ ትኩረት በመስጠት የእናቶችን ሞት ትርጉም ባለዉ መልኩ ለመቀነስ የሚደረገዉን ርብርብ ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በፕሮግራም ማስተዋወቂያ መድረኩ ላይ በቀረበዉ መረጃ መሰረት፡- በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት 17 በመቶ ወጣቶች ያለዕድሜ የሚያረግዙ መሆኑን፣ በሀገራችን ኢትዮጲያ ደግሞ 13 በመቶ ያህል ያለ ዕድሜ እርግዝና መኖሩንና ዕድሜያቸው 18 ዓመት ሳይሞላቸዉ ወደ ጋብቻ የሚገቡ ወጣቶች 40 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልፀዉ ይህም ዕድሜያቸዉ ከ15-19 የሆናቸዉ አፍላ ወጣቶች ላይ ያተኮረ ስራ ለመስራት አስገዳጅ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በፕሮግራም ማስተዋወቂያ መድረኩ ላይ የክልሉ ጤና ቢሮ አመራሮችና ባለሙያዎች፣ፕሮግራሙ የሚጀመርባቸዉ የዞንና ወረዳ ጤና ሃላፊዎች፣ እንዲሁም የማሪስቶፕስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ እና የአለም አቀፍ የህዝብ አገልግሎት የስራ ሃፊዎችና ባለሙያዎች በተገኙበት ሰፊ ዉይይት የተደረገ ሲሆን በአፍላ ወጣቶች ላይ በተለይም በገጠር ያገቡ ወጣት ሴቶች ላይ ያተኮረ የስነተዋልዶ ጤናና የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ፕሮግራሙ ሲጀመር የግብአት ችግር እንዳይገጥም ከወዲሁ ማሰብ፣ ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃትን ለመከላከል እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት የሚሰሩ ስራዎች አቀናጅቶ መስራት ተገቢ መሆኑን በአስተያየታቸዉ ጠቁመዋል ፡፡