ጥራቱን የጠበቀ ዘላቂ የክትባት ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ተገልጿል

በአገራችን የክትባት ስራዎች ከተጀመሩ ረጅም ዓመታትን ማስቆጠራቸው እና በነዚህ ዓመታትም በተከናወነው የክትባት ፕሮግራም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህጻናትንና የህብረተሰብ ክፍሎችን ህይወት መታደግ ተችሏል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጥራቱን የጠበቀ ዘላቂ የክትባት ሥርዓት በመዘርጋት በክትባት መከላከል በሚቻላቸው በሽታዎች ሳቢያ የሚከሰት ህመምና ሞት መቀነስ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መንግስት ጤና ቢሮ ከጤና ልማት አጋር ድርጅት ከሆነው የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ጋር በጥምረት ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ መገለፁ ታውቌል፡፡

የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/ መንግስት ጤና ቢሮ የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በመልዕክታቸው ጥራቱን የጠበቀ ዘላቂ የሆነ የክትባት ሥርዓትን ተደራሽነትን በማረጋገጥ የኩፍኝ ፣ የፖሊዮ፣ የቢጫ ወባ፣ ወረርሽኝና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ስርጭትን መግታት እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

በክትባት መከላከል በሚቻላቸው በሽታዎች ሳቢያ የሚከሰት ህመምና ሞት መቀነስ እንዲሁም ጥራትን ከተደራሽነት አጣምሮ ተግባርን መፈፀም የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን እንደሚገባው እና መከላከል በሚቻሉ የጤና እክሎች የእናቶች እና የሕፃናት ሕይወት እንዳይጠፋ በትኩረት መስራት አማራጭ የሌለው ተግባር ተደርጎ ሊወስድ እንደሚገባ አቶ ማሙሽ ሁሴን ተናግረዋል ።

በጋራ የውይይት መድረኩ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ሳቢያ ለሚያጋጥሙ የጤና እክሎች ፈጣን የሆኑ ምላሾችን እየሰጡ ከመሄድ አንፃር የተስተዋሉ ተግባራትን በጥንካሬ አንስቷቸዋል በሌላው መልኩ በጉድለት የተገመገመው የዘመነ የመረጃ አያያዝና አጠቃቀምን ማጎልበት፣ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

የማህበረሰቡን የጤና አግልግሎት ለማሻሻል የክትባት ተደራሽነትን ለሁሉም በማዳረስ ረገድ የተከናወኑ ተግባራት፣ ያጋጠሙ ትግዳሮቶች፣ በቀጣይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚያግዙ ሃሳቦችን የማመላከት እና ወደ ተግባር ማስገባትን ታላሚ አድርጎ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ከክልሉ ጤና ቢሮ፣ ከዞንና ፣ ከልዩ ወረዳ ፣ ከጤና ልማት አጋር ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/ መንግስት ጤና ቢሮ