አራቱን የወባ መከላከያ ስትራቴጂዎች በአግባቡ በመተግበር የወባ በሽታ ጫናን መቀነስ ይቻላል

በክልሉ ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበት ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር የሆኑት አቶ ማሌ ማቴ የወባ ሳምንት ይፋዊ ማስጀመሪያ መርሀ-ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የወባ በሽታ በማህበረሰቡ ላይ የሚያሳድረዉን ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ስነልቦናዊ ጫና መቀነስ የሚቻለዉ ሁሉን አቀፍ የቁጥጥርና ክትትል ተግባራት በማጠናከር እንደሆነ ገልፀዉ በተለይም 4ቱን የመከላከያ ስትራቴጂዎች ማለትም፡- የአካባቢ ቁጥጥር ስራን በማጠናከር፣ አጎበርን በአግባቡና በትክክለኛዉ መንገድ በመጠቀም፣የኬሚካል ርጭት በማከናወን እንዲሁም የህመም ስሜት ሲኖር በአስቸኳይ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ህክምና በማድረግ በሽታዉን መከላከል እንደሚቻል ጠቁመዉ ለዚህም መላዉን ህብረተሰብ ያሳተፈ ንቅናቄ መፍጠር ስለሚገባ ከቀበሌ እስከ ክልል ያለዉ አመራር ለችግሩ ግዝፈት ምላሽ የሚሰጥ ስራ ይጠበቅበታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በዚሁ ጊዜ የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መ ጤና ቢሮ የህዝብ ግንኙነትና ጤና ኮምዩኒክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቀድረላህ አህመድ እንደተናገሩት የወባ በሽታ ለበርካታ አመታት የሀገራችን ብሎም የክልላችን ዋነኛ የህብረተሰብ ጤና ችግር በመሆኑ ለከመላከሉ ስራ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ አስታዉሰዉ ከ65 በመቶ የሚሆነዉ የክልሉ ህብረተሰብ ወባማ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖር በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የራሳቸዉ ጉዳይ አድርገዉ በሽታዉን ለመከላከል ብሎም ጨርሶ ለማትፋት ሊረባረቡ እንደሚገባ፤ በተለይም የሚዲያ ተቋማት ለህዝቡ መረጃ በመስጠትና ግንዛቤን በማስፋት የተጣለባቸዉን ማህበራዊ ግዴታ ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በዕለቱ የዳይሬክቶሬቱ ከፍተኛ ባለሙያ በሆኑት አቶ ሄኖክ ስለ ወባ በሸታ ታሪካዊ ዳራ፣ባሳደረዉ አሉታዊ ጫናና ነባራዊ ሁኔታ እና በቀጣይ በሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያ ሰነድ አቅርበዉ ሰፊ ዉይይት ተደርጎበታል፡፡

ዘገባ በቢሮዉ የህዝብ ግንኙነትና ኮምዩኒኬሽን ነዉ፤