የደ/ብ/ብ/ህ/ ክልል ምክር ቤት እና የክልሉ ጤና ቢሮ በየደረጃው ከሚገኙ አፈ-ጉባኤ እና ከማህበራዊ ዘርፍ ሴቶችና ህፃናት ቋሚ ኮሚቴ ጋር በወቅታዊ የጤና ችግሮች ላይ ተወያዩ፤

የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤን ጨምሮ የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ አቅናው ካውዛ እና የማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች በተገኙበት በኮቪድ19 የመከላከል ተግባራት ላይ ወቅታዊ መረጃ ያቀረቡት የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተከናወኑ የአደጋ ጊዜ ተግባቦትና የማህበረሰብ ተሳትፎ ስራዎች፣ የበሽታ ቅኝትና ምላሽ አሰጣጥ ተግባራት እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር በተከናወኑ ስራዎች ላይ ሰፊ መረጃ አቅርበው፦

በማህበረሰብ ደረጃ በሚደረጉ የጥንቃቄ ተግባራት መቀዛቀዝ ሳቢያ ቫይረሱ በማህበረሰቡ ውስጥ እየተዛመተ በመምጣቱ በከተማም ሆነ በገጠር በቫይረሱ የሚያዙና የሚሞቱ ወገኖች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑን አመላክተዋል።

ዳይሬክተሩ አያይዘውም በክልሉ የምርመራ ማዕከላት ቁጥር ቢጨምርም የሚመረምሩት ናሙና ቁጥር ዝቅተኛ በመሆኑ በክልሉ ትክክለኛውን የቫይረሱን ምጣኔ ለማወቅ አዳጋች እንደሆነ ጠቁመዋል።

በተለይም በክልሉ ውስጥ ካሉ 193 ወረዳዎች ውስጥ 166 ወረዳዎች በበሽታው እንደተጠቁ ገልፀው፦ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦ ፣ደቡብ ኦሞ፣ ጉራጌ ከፍተኛ ቁጥር የተመዘገበባቸው ዞኖች እንደሆኑና የቫይረሱን ትክክለኛ የስርጭት መጠን ለማወቅ በሁሉም አካባቢዎች የምርመራ አቅምን ማሳደግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

አቶ ማሙሽ በገለፃቸው ቫይረሱ ይበልጥ አምራች የሆኑ ወጣት ሀይሎችን በአማካይ 29 ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉት ላይ በስፋት እንደተገኘ ጠቁመው አስካሁን በክልሉ 27 ሰዎች በቫይረሱ እንደሞቱ ፣ 488 የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነና ከነዚህም ውስጥ 482ቱ ምንም አይነት የህመሙ ምልክት እስካሁን እንዳልታየባቸው በሪፖርታቸው ጠቁመዋል ።