የወባ በሽታ የሚያስከትላቸውን መጠነ ሰፊ ችግሮች ለመቀነስ የባለድርሻ አካላት ሚና የጎላ ሊሆን ይገባል

በዛሬው ዕለት “ወባን ማጥፋት ከኔ ይጀምራል ” በሚል መሪ ቃል የወባ ሳምንት ይፋዊ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ጀምሯል ።
በዚሁ ጊዜ የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መ ጤና ቢሮ ምክትል እና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ሀላፊ አቶ መና መኩሪያ በመልዕክታቸው በወባ ምክንያት የሚከሰተውን የበሽታ ጫናና የሞት ምጣኔ ለመቀነስ መንግስትና ባለድርሻ አካላት ባደረጉት ርብርብ አመርቂ ውጤት ተመዝግቦ እንደነበር አስታውሰው፦
በዚህ ተስፋ ሰጪ ውጤት መነሻ ወባን ጨርሶ ለማስወገድ በክልሉ ከ100 ወረዳዎች በላይ በፕሮግራሙ ተካተው እየተሰራባቸው ቢሆንም በተለያዩ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች በተቀመጠው ጊዜ እውን ለማድረግ ፈታኝ ቢሆንም በ2030 ሁሉም ቀበሌና ወረዳዎች በሽታውን በማስወገድ ቅኝት ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ሃላፊው አያይዘውም የወባ መከላከል እና ጨርሶ የማስወገድ ስራ በጤናው ሴክተር ብቻ የሚከናወን ባለመሆኑ የተለያዩ ሴክተር ቢሮዎች፣ የሀይማኖት ተቋማት ፣ብዙሃን መገናኛዎች ፣ የወባ መከላከል እና ማጥፋት ማህበር እንዲሁም አጋር ድርጅቶች ከወትሮው በተሻለ ድጋፍ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ በአደራም ጭምር አሳስበዋል ።

በወባ ሳምንት ይፋዊ ማስጀመሪያ መርሀ -ግብር ላይ እስካሁን በወባ በሽታ መከላከል እና ቁጥጥር ስራውን አስመልክቶ በባለሙያዎች ሰነድ ቀርቦ አጠቃላይ ውይይት እንደሚደረግበት ይጠበቃል ።

ዘገባ በቢሮው የህዝብ ግንኙነትና ጤና ኮምዩኒኬሽን ነው