የዘመነ የጤና መረጃ ትግበራን ማጠናከር ከመረጃ ጥራት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ለመቀነስ አቅም እንዳለው ተገለፀ

የዘመነ የጤና መረጃ ትግበራን ማጠናከር ከመረጃ ጥራት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ለመቀነስ አቅም እንዳለው ተገለፀ የዘመነ የጤና መረጃ ትግበራን ማጠናከር ከመረጃ አያያዝ፣ አጠቃቀምና ለውሳኔ ከመጠቀም ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመቀነስ እንደሚያግዝ ለ5 ተከታታይ ቀናት በወላይታ ሶዶ ከተማ ስካሄድ በቆየው የ2015 ዓ.ም ወረዳን መሠረት ባደረገው የስልጠና ማጠቃለያ ላይ መገለፁን የ/ደ/ብ/ብ/ብ/ሕ /ክ /መንግስት ጤና ቢሮ አስታውቋል ። በስልጠናው ከሁሉም ዞኖችና ከልዩ ወረዳዎች የተወጣጡ ከፍተኛ የዕቅድና የፕሮግራም ዘርፍ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል ይህም ያለን ልምድ ና ዕውቀት በሰፊው በመጠቀም በትግበራ ወቅት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች በመጠቆም፣ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ጭምር በማመላከት የህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ተብራርቷል ። ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በቀጣይ ሁለት ተከታታይ ሳምንታትም ዕቅዱን በሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ማወረድ አንዱ የስምምነት አካል መሆኑ ታውቋል። ወረዳን መሠረት ያደረገውን የጤና ዕቅድ በሶፍትዌር የታገዘ መሆኑ መረጃን በማዘመን ፍትዓዊና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ እንደሚያግዝ ተብራርቷል ። ይሁን እንጂ ለዕቅዱ ውጤታማነት፣ ከሰው ሐይል፣ ከኔት ወርክ መዘግየትና መቆራረጥ ፣እንዲሁም ቴክኖሎጂውን ሊደግፉ በሚችሉ መሳሪያዎች አቅርቦት አጠቃቀም ብሎም መረጃውን በተገቢው ከመመገብ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በየደረጃው እየቀረፉ መሄድ ተጠባቂ መሆኑ ተመላክቷል።
በመጨረሻም ወረዳን መሰረት ያደረገው ዕቅድ በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ በሁሉም መዋቅሮች ተጠናቆ ለጤና ሚኒስትር የሚቀርብ መሆኑ ተገልጿል ።
የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መንግስት ጤና ቢሮ