የወባ በሽታ ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ አፉጣኝ ዕርምጃ እንዲወሰድ ተጠየቀ

የወባ በሽታ ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ ስርጭቱን የመከላከል እና የመቆጣጠር ተግባር ልዩ ትኩረት በአምስት ዞኖችና በሁለት ልዩ ወረዳዎች ትኩረት ተደርጎ በመስራት ላይ መሆኑን የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መንግስት ጤና ቢሮ አስታውቋል ።

ቢሮው የወባ በሽታ በህብረተሰቡ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጫና ለመቀነስ እንዲያስችል በወላይታ፣ ጋሞ፣ ዳውሮ ፣ ደ/ኦሞና ጎፋ ዞኖችና ባስኬቶና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች ከዚህ ቀደም ከነበረው ተመሳሳይ ወቅት አኳያ የወባ በሽታ ጫና የሰፋባቸው በመሆኑ በመደረግ ላይ ያለው ርብርብ ከወላይታ ዞን በስተቀር ስራው ተገቢው ትኩረት ያልተሰጠው በመሆኑ በህብረተሰቡ ከዚህ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ስራውን በቅንጅት መፈጸም ይገባል ።

የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል የቢሮ ሃላፊ የፕሮግራሞች ዘርፍ ሃላፊ አቶ መና መኩሪያ በተለያዩ ጊዜያት የወባ በሽታ ስርጭትን ለመግታትና የሕብረተሰቡ የጤና ችግር እንዳይሆን የተለያዩ ተግባራት ተከናውነው ውጤቶችም የተመዘገቡ ቢሆንም በአሁኑ በተጠቀሱት አካባቢዎች ላይ የወባ ስርጭት ከሌሎች ጊዜያት ጋር ሲነፃፀር መጨመሩን ተናግረው አመራሩ፣ ባለሙያ እና ባለሙያው ህብረተሰቡን አስተባብሮ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ርብርብ የሚያሻው መሆኑን ያመላክታል ብለዋል።

በወባ መከላከልና መቆጣጠር ረገድ ያሉ ተሞክሮችን መጠቀም ፣ በተለይ የወባ በሽታ ይበልጥ የሚከሰትባቸውን አካባቢዎች በመለየት ልዩ ትኩረት መስጠት ፣ የኬሚካል ርጭት፣ የአጎበር አቅርቦትና የአከባቢ ቁጥጥር ስራዎችን ማጠናከር ተግባራትን በሁሉም ወባማ አከባቢዎች ለማስቀጠል በዚሁ ሳቢያ የሚከሰትን የጤና ቀውስ መቀነስ እንደሚገባ ተመልክቷል ።

ዛሬ ከላይ የተጠቀሱ ዞኖችንና ልዩ ወረዳዎችን የወባ መከላከልና መቆጣጠር ስራቸውን ለመገምገም በተጠራው መድረክ በወላይታ ዞን የወባ በሽታ ከወትሮው በተለየ መልኩ ማሻቀቡን በመገምገም በዞኑ እስከታችኛው አካል ድረስ በቁርጠኝነትና በቅንጅት በተደረገው ሰፊ እርብርቦሽ በሽታውን በቁጥጥር ስር ማዋል የተቻለ መሆኑ ተጠቅሷል፤ በተለይ በቦሎሶ ቦምቤ ወረዳ በአንድ ክላስተር ብቻ ከ2800 በላይ የነበረውን የታማሚ ቁጥር በአንድ ወር ውስጥ በተደረገው ርብርብ ቀጥሩን ከ300 በታች ማድረስ መቻሉ በመልካም ተሞክሮነት ተገልጿል።
በአንጻሩ በተቀሩት አራት ዞኖችና ሁለቱ ልዩ ወረዳዎች እየተደረገ ያለው የወባ በሽታ መከላከል ስራው በተደረገው የግብዓት አቅርቦት ልክና ከተፈጠረው የወባ በሽታ ጫና አኳያ ውጤታማ ያልሆነ ውጤት ስለሆነ የሚታየው ህብረተሰቡ ለከፋ ችግር ከመጋለጡ በፊት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባቀናጀና ባሳተፈ መልኩ ርብርብ ሊደረግ ይገባል ተብሎ በተለይ ህብረተሰቡን በማስተባበር እና በማነቃነቅ ሊፈጸም ይገባል ተብሎ ተጠቅሷል ።