የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያና ሪፌራል ሆስፒታል የዐይን ሕክምና ማዕከል አሁንም አገልግሎቱን በማስፋት ቀጥሏል

በ2002 ዓ.ም ላይት ፎር ዜ ዎርልድ ከተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ ተገንብቶ የተደራጀ የዓይን ሕክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያና ሪፌራል ሆስፒታል የዓይን ሕክምና ማዕከል ለማህበረሰቡ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። ከእነዚህ አገልግሎቶች መካከል የዓይን ጤንነት ምርመራና ክትትል፣ የመነጽር ችግር መለካትን የመሳሰሉ አገልግሎቶች ተጠቃሽ ናቸው። ማዕከሉ የተመላላሽና ተኝቶ ሕክምና አገልግሎቶችን ጨምሮ የተደራጀ መለስተኛና አጠቃላይ ቀዶ ጥገና አገልግሎት ስፔሻሊስት ሀኪሞችን ጨምሮ በእውቀት፣ ልምድና በሙያው በተካኑ ባለሙያዎች በመታገዝ ጥራት ያለው አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። የዓይን ግፊት ማስተካከያ ቀዶ ጥገና እና የዓይን ሽፋሽፍት ቀዶ ጥገናዎችን ጨምሮ ሌሎች ደንገተኛ የዓይን ቀዶ ጥገናዎች በማዕከሉ ከሚሰጡ የቀዶ ጥገና ህክምናዎች የሚጠቀሱ ናቸው። ማዕከሉ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ጥምረት በመፍጠር ዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የማህበረሰብ አካላትን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነፃ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገናን ጨምሮ ሌሎች ከዓይን ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የሕክምና አገልግሎቶችን በዘመቻ መልክ በመስጠት ላይ ይገኛል። ይህም በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ሕክምና ማገኘት ላልቻሉና ለዓመታት ብርሃን ሳያዩ ለቆዩ ወገኖች እንደ መልካም አጋጣሚ የሚታይ ተግባር ሲሆን ብዙዎችን ተጠቃሚ ከማድረጉም ባሻገር ዳግም ብርሃን እንዲያዩ አድርጓል። ማዕከሉ ላለፉት ሶስት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና ያጠናቀቀ ሲሆን ከወላይታ እና አጎራባች ዞኖች የመጡ በቁጥር 48 ሰዎች ተጠቃሚ ሆነዋል። ከእነዚህ መካከል 43ቱ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና እንዲሁም 5ቱ ከዓይን ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሌሎች የሕክምና አገልግሎቶችን ተጠቃሚ አድርጓል።

ምንጭ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያና ሪፌራል ሆስፒታል

የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መንግስት ጤና ቢሮ