የኮቪድ19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የፍትህና የፀጥታ አካላት ሚና ከፍተኛ ሊሆን ይገባል

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በአለም ላይ ብሎም በሀገራችን በተከሰተበት የመጀመሪያ ወራት አካባቢ ወረርሽኙ ለመከላከልና ለቆጣጠር የፍትህና የፀጥታ አካላት ሲያከናዉኑ የነበረዉን የተቀናጀ አሰራር በማጠናከር እየከፋ የመጣዉን የወረርሽኙን ጫና መቀነስ እንደሚገባ የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መ ጤና ቢሮና የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ከፍትህና ከፀጥታ አካላት ጋር ባደረጉት የጋራ የምክክር መድረክ ላይ ተጠቁሟል፡፡
የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለፁት ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከክልል ርዕሰ መስተዳደር ጀምሮ እስከ ታችኛዉ መዋቅር ድረስ በተጠናከረና በተናበበ መልኩ መመራት በመቻሉ በክልሉ ቫይረሱ ሊያደርስ የሚችለዉን ጉዳት መቀነስ መቻሉን ጠቁመዉ በአሁኑ ወቅት በማህበረሰቡ ዉስጥ እየተስተዋለ ያለዉ መዘናጋት በዚሁ ከቀጠለ የከፋ ችግር ሊያስከትል ስለሚችል አመራሩ፣የፍትህና የፀጥታ አካላት እንዲሁም የጤና ባለሙያዉ ተቀናጅተዉ ሊሰሩ እንደሚገባ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡
በሽታዉን አቅልሎ ማየት፣መከላከያ እርምጃዎቹን ለመተግበር መሰላቸት፣ስራዉን እንደዘመቻ በመቁጠርና ተቋማዊ አለማድረግ በጉድለት የተለዩ ጉዳዮች መሆናቸዉን ጠቁመዉ የፖለቲካ አመራሩ ለጉዳዩ ትኩረት በሰጠበት አካባቢ ሁሉ የህብረተሰቡም ተሳትፎ የላቀ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ በባለሙያዎች በቀረቡ ወቅታዊ ፅሁፎች መነሻ አሁንም የወርርሽኑ አሳሳቢነት የተጠቆመ ሲሆን፤ የክልሉ ፖሊስ ኮምሽን ኮምሽነር ነብዩ ኢሳያስ በበኩላቸዉ ህብረተሰቡ ስለቫይረሱ ያለዉን ዕዉቀት ማሳደግ እና ያለዉን የተሳሳተ አመለካከት ማረም ተቀዳሚ ተግባር መሆኑን ጠቁመዉ፤ ሆን ብለዉ የመከላከያ እርምጃዎችን በማይተገብሩና ለሌሎች በቫይረሱ መያዝ ምክንያት በሚሆኑ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችልም አሳስበዋል፡፡
በክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሮ ምክትል ዋና አቃቤ ህግ አቶ ሶፎኒያስ ደስታ የኮቪድ19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጣዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳቱን ተከትሎ በበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የታየዉ መዘናጋት ትክክል አለመሆኑን ጠቁመዉ፤ አዋጁ ቢነሳም በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የኮቪድ መከላከልና መቆጣጠር መመሪያ ቁጥር 30/2013 ላይ የተካተቱ አስገዳጅ ሁኔታዎችን በመፈፀምና በማስፈፀም የማህበረሰቡን የወርሽኝ ተጋላጭነት መቀነስ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በዚሁ ጊዜ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በመመሪያዉ ላይ በሀይማኖታዊ ስነስርዓት እና ማህበራዊ ዝግጅቶች፤የቀብር ስነ ስርአት እና የሀዘን ስነ ስርአት፣በቤት ውስጥ ማቆያ እና ክብካቤ ወቅት እንዲሁም በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ መደረግ ስለሚገባዉ ጥንቃቄ የተቀመጡ ሀሳቦችን በመተግበርና በማስተግበር እንዲሁም የህግ ተጠያቂነትን ባማከለ መልኩ የተከለከሉ ተግባራትንና የተጣሉ ግዴታዎችን ሁሉም ዜጋ እንዲተገብር የህግ አስከባሪዉ ትልቅ ሃላፊነት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ኮምዩኒኬሽን ዳሬክቶሬት