የኮቪድ-19 ማጠናከሪያ ክትባት ሆስፒታል የመግባት መጠንን እንደሚቀንስ ጥናት አመለከተ

የኮቪድ-19 ማጠናከሪያ ሦስተኛ ክትባት ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው ወደ ሆስፒታል እንዳይገቡ ለመከላከል 88 በመቶ በማገዝ ውጤታማ ነው ሲል የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የጤና ጥበቃ ኤጀንሲ አዲስ ጥናት አመለከተ። አስትራዜኒካ፣ ፋይዘር ወይም ሞደርና ክትባቶችን ሁለት ዙር የወሰዱ ሰዎች በኦሚክሮን እንዳይያዙ እምብዛም ባይጠብቃቸውም በጠና ከመታመም እንደሚከላከል ጥናቱ ያሳያል። የጤና ኃላፊዎችም ይህ ጥናት ሦስተኛ ዙር ወይም የማጠናከሪያ ክትባት አስፈላጊነትን ያጎላዋል ሲሉ ተናግረዋል። የዩኬ የጤና ፀሐፊው ሳጂድ ጃቪድ “ይህ ክትባቶች ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ የሚያረጋግጥ እና የበለጠ ተስፋ ሰጪ መረጃ ነው። ሕይወትን ያድናል እንዲሁም ከባድ በሽታን ይከላከላል” ሲሉ ተናግረዋል። “ይህ ሳይንሳዊ ትንታኔ ክትባቱን ያልወሰዳችሁ እንደሆነ በኮቪድ-19 ምክንያት ወደ ሆስፒታል የመሄድ ዕድላችሁ እስከ ስምንት እጥፍ ከፍ ያለ መሆኑን ያሳያል” ሲሉም አስጠንቅቀዋል። የዩኬ የጤና ደኅንነት ኤጀንሲ በሠራው በዚህ ጥናቱ ላይ ከ600,000 በላይ የተረጋገጡ እና የተጠረጠሩ በኦሚክሮን የተያዙ ሰዎችን መረጃ በመተንተን ነው ድምዳሜ ላይ የደረሰው። እንደ ኤጀንሲው ግኝት ከሆን አንድ ዙር የክትባት መጠን የሆስፒታል ሕክምና የሚያስፈልገው ሕመምን በ52 በመቶ ቀንሶታል። ሁለተኛውን ዙር ክትባት መውሰድ ደግሞ ይህንን የመከላከል መጠን ወደ 72 በመቶ ከፍ የሚያደርገው ሲሆን ከ25 ሳምንት በኋላ ይህ የመከላከል አቅም መልሶ ወደ 52 በመቶ ዝቅ እንደሚል ታውቋል። ነገር ግን ሦስተኛው ዙር ክትባት ከተወሰደ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ይህ በሆስፒታል የመተኛትን የመከላከል አቅም ወደ 88 በመቶ ከፍ ብሏል። የኤጀንሲው ጥናት ይህ ጥበቃ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ለማወቅ እስካሁን በቂ መረጃ አለመገኘቱን ነገር ግን ሕመምን በመቀነስ ረገድ ረዘም ላለ ጊዜ እንደሚሠራ ይፋ አድርጓል። ቀደም ሲል የኮቪድ-19 ሕመም ምልክቶች በታየባቸው ሰዎች ላይ ደግሞ ከእያንዳንዱ ዙር ክትባት በኋላ ያለው የመከላከል መጠን ካልተከተቡ ሰዎች ጋር ሲነጻጸር 68 በመቶ ያህል ያነሰ መሆኑም ታውቋል። ከካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ የተደረገው ሁለተኛ ጥናት አንድ ሰው በኦሚክሮን ከተያዘ በኋላ ሆስፒታል የመግባት ስጋት ከዴልታ ዝርያ ጋር ሲነጻጸር በግማሽ ያህል ያነሰ እንደሆነ አረጋግጧል።
ምንጭ @tenamereja
የደ/ብ/ብ/ሕ /ክ/መንግስት ጤና ቢሮ