የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን ለመከላከል እንዲሁም በዚሁ ሳቢያ በሰው ህይወት ላይ ሊከሰት የሚችለውን ህመምና ሞትን ለመቀነስ የሚያግዝ ሁለት ሚሊየን ብር የሚገመት መድሃኒቶችና የህክምና መገልገያ ግብዓት ድጋፍ ከዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ድጋፍ እንደተደረገለት የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መንግስት ጤና ቢሮ የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት አስታውቌል፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰቱ የሚችሉ ድንገተኛ አደጋዎችንና የጤና ስጋቶችን ለመቋቋም ተግባራዊ ምላሽን ለማረጋገጥ ከበጀት አንጻር 240 ሚሊየን(ሁለት መቶ አርባ ሚሊየን ብር ) ገደማ እንደሚጠበቅ የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መንግስት ጤና ቢሮ የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን ተናግረዋል፡፡ በተለይም ድርቁን ተከትለው ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎች ፣ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት፣ የወባ በሽታ ስርጭት ፣የኮሌራ ክስተት፣ እንዲሁም የማጅራት ገትር በሽታዎች በስጋትነት ተይዘው ይህንንም ተግባራዊ ምላሽ ለማረጋገጥ የጤና ልማት አጋሮችን ያማከለ ውይይት ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱን በመግለጽ የዛሬውም ድጋፍ የዚሁ አካል መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን አክለውም የተከናወኑና በመከናወን ላይ ያሉ አበረታች ድጋፎች ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው መሆኑን አውስተው መንግስት የሚያከናዉናቸዉን የጤና ልማት ስራዎችን ለመደገፍ በተለያዩ ፕሮግራሞች በመስራት ላይ ያሉ አጋር ድርጅቶችም በዚህ ተግባር ሊሣተፉ እንደሚገባ በመጠቆም የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ላደረገው ድጋፍ ለሰጠው ፈጣን ምላሽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) በደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መንግስት ጤና ቢሮ እና በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ዶ/ር በረከት ያለው በበኩላቸው በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት የጤና ልማት አጋር ድርጅት የሆነው የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የመንግስትን አቅጣጫዎችና ፖሊሲዎችን በተከተለ መልኩ በተለያዩ የጤና ልማት ስራዎችን እንደሚደግፍ በመግለጽ ድርቁን ተከትለው ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ቀውሶችን ለመቅረፍ ታላሚ ያደረጉ መድሃኒቶችና የህክምና መገልገያ ግብዓት መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ /መንግስት ጤና ቢሮ