የክልሉ ጤና ቢሮ ለአዲስና ነባር ሆስፒታሎች ማስፋፊያ የውል ስምምነት መፈራረሙን አስታወቀ፡፡

ጤና ለሀገራችን ዕድገትና ለሕብረተሰባችን ደህንነት መረጋገጥ ወሳኝ ከሆኑት ማህበራዊ ልማት ዘርፎች አንዱ እንደ መሆኑ መጠን ህብረተሰቡ የጤና አገልግሎት ሽፋን ካለበት ደረጃ ከፍ የማድረግ ሥራ ሲከናወን የጤና ተቋማትን ግንባታ ማረጋገጥ ተጠባቂ ያደርገዋል ፣የግንባታ ሥራው መዘግየት ፤መቋረጥ እንዲሁም ተገቢውን አገልግሎት መስጠት አለመቻል የመልካም አስተዳደር ጥያቄን በጊዜው ያስነሳል በመሆኑም መሰል የህዝብ ጥያቄን ሲያስነሱ ለነበሩ የጤና ተቋማት ግንባታ ምላሽ ሚሆን ውል ስምምነት መፈራረሙን የ/ደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/ መንግስት ጤና ቢሮ አስታውቋል፡፡

የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/ መንግስት ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ አቅናው ካውዛ ሆስፒታሎቹ ግንባታቸው ለረጅም ግዜያት መቋረጡንና ሳይጠናቀቅ መቅረቱን ለዚህም የውጭ ምንዛሪ ዋጋ መጨመር በምክንያትነት እንደሚጠቀስ ተናግረው በጅምር የቀሩ ሆስፒታሎችን ለማጠናቀቅና ለማስፋፋት ከመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች መካከል በቡርጂ ልዩ ወረዳ ፣ሶያማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ በጋሞ ዞን የዘፍኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ ደቡብ ኦሞ ዞን ቱርሚ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ ሲጠቀሱ ሳውላ እና ሀለባ ቁሊቶ አጠቃላይ ሆስፒታሎች በማስፋፊያ ፕሮጀክቱ መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡

የጊዶሌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በተመለከተ በአዲስ ማስፍፊያ ግንባታን ለማስጀመር የሚያስችል የውል ስምምነት መደረጉን ተናግረው ሆስፒታሎች በተቀመጠላቸው የግዜ ገደብ ተጠናቀው ተገቢውን የጤና አገልግሎትን ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንዲችሉ ሁሉም የበኩሉን ሃላፊነት መወጣት እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡

ከተቋራጭ ድርጅቶች ስራ አስኪያጅ አቶ ወንድም አገኝ በቀለ በበኩላቸው ሶያማ የመጀመሪያ ሆስፒታልን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ የሚፈለገውን ጥራት ጠብቆ ለማጠናቀቅ እንዲቻል ድርጅታቸው ዝግጁ መሆኑን በማንሳት የፀጥታ ሁኔታ ፣ ለክልሉ ለሚቀርቡ የክፍያ ጥያቄዎችን በወቅቱ አለመፈፀም፣ እንዲሁም በልዩ ወረዳ ደረጃ ከይዞታ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎችን በጋራ እየፈቱ መሄድ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
የሀላባ ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ አለማየሁ ጌታቸው በበኩላቸወ የሀላባ ቁሊቶ አጠቃላይ ሆስፒታል የማስፋፊያ ፕሮጀክት በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ተገንብቶ ለህብረተሰቡ አስፈላጊውን አገልግሎት መስጠት እንዲችል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/ መንግስት ጤና ቢሮ