የእናቶችንና የጨቅላ ሕፃናት ሞትን ለመቀነስ አገልግሎት መስጫ ህንፃዎች ግንባታ ምረቃና ርክክብ ስራ ተከናወነ

በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክ/መንግስት ጤና ቢሮ ከትራንስፎርም ፒኤችሲ የደቡብ ክልል ፕሮጄክትጋር በመተባበር እና ከጤና ተቋማት ጋር በመቀናጀት የእናቶችና ሕፃናት አገልግሎት መስጫ ህንፃ ግንባታ በማከናወን ለደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክ/መንግስት ለሀላባና ለከምባታ ጠምባሮ ዞኖች ሁለት ወረዳዎች አስረክበዋል፡፡ የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አቅናው ካውዛ በህንጻዎቹ ርክብክብ ወቅት ባደረጉት ንግግር በነባር ጤና ጣቢያች ውስጥ የማዋለጃ እና የእናቶች ክብካቤ ማዕከላት ደረጃቸውን ያልጠበቁ መሆናቸው እንዲሁም የወሊድ አገልግሎቱና ተያያዥ አገልግሎቶች አንጻር ከተፈጠረው ተጨማሪ ጥያቄ አኳያ እስከታች ከሴቶች ልማት ቡድን ጀምሮ የንቅናቄ ስራዎችን የተሰራት ሲሆን ይህንን ስራ አመራሩ በባለቤትነት በመስራቱና ህዝቡንም ማሳተፍ በመቻሉ የመጡ ውጤቶች መሆናቸውን ጠቅሰው አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ያሉ ክፍተቶች ሰፋ ያሉ በመሆናቸው ችግሮቹን ለመቅረፍ ይኸው ግንባታ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፤ እናቶችን ከወሊድ በፊትና በኋላ መንከባከብና ማቆየት ወሳኝ በመሆኑ ከዚህ በፊት በቂ የማቆያ ቦታ ባለመኖሩ ለእንግልት ተዳርገው የነበረ ሲሆን በአዲሱ ህንፃ እናቶችን ማቆየት በመቻሉ የእናቶችንና የጨቅላ ሕፃናት ሞትን ለመቀነስ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ከፍተዋል፡፡ የጤና ተቋማት ከፍተኛ አፈፃፀም እንዲኖራቸው ለማድረግ እና በዚሁም ከጤና ትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች አንዱ የሆነውን የወረዳ ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ እንዲያስችል የጤና ተቋማትን የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራ ወሳኝ በመሆኑ ትራንሰፎርም ፒኤችሲ የደቡብ ክልል ፕሮጄክት ተግባሩ እንዲሳካ በማድረግ በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክ/መንግስት ጤና ቢሮ በኩል ለዞኖቹ ማስረከብ ችለዋል፡፡ ትራንሰፎርም ፒኤችሲ የደቡብ ክልል ፕሮጄክት የወረዳን ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ለማሳካት ቴክኒካዊና ፋይናንሺያል ድጋፍ በማድረግ የድጋፍና ክትትሉንም ስራ በማጠናከር ባደረገው ጥረት የእናቶችና ህጻናት ጤና አገልግሎት መስጫ ሕንፃ በመገንባት በአቶቲ ኡሎ ወረዳ አስተዳዳር፣ እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ የአለም አቀፍ ወረርሺኝ ከሆነው የኮሮና ቫይረስ ራሱን በአግባቡ እየተከላከለ ተቋሙን የመደገፍና በባለቤትነት መንከባከብ ስራ እንዲያከናውንበት እንዲቻል በርክብክብ ስራው ወቅት መግለጽ ተችሏል፡፡ ግንባታው በዚህ መልኩ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱን የክልል፣ የዞን፣ የወረዳ አመራርና ባለሙያዎች፤ እንዲሁም የUSAID Transform PHC አመራርና ባለሙያዎች፣ ግንባታውን ላከናወኑ የግንባታ ባለሙያዎች የጤና ጣቢያው ባለሙያዎች የላቀ ምስጋና በማቅረብ ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት በቀጣይነት እንደሚሰጥ የከምባታ ጠንባሮ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ የሆኑት አቶ መልካሙ ገብሬ ገልፀዋል፡፡ በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልል በሀላባ እና ዳንቦያ በተገነባው ግንባታ መሰረት በቀጣይ በተመሳሳይ መልኩ በዳውሮ ዞን፣ በካፋ ዞን፣ በደቡብ ኦሞ ዞኖችና በደራሼ ልዩ ወረዳ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ግንባታዎች የሚገነቡ መሆናቸውን የUSAID Transform PHC በአገራቀፍ ደረጃ ዋና አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር መንግስቱ አስናቀ አስታውቀዋል፡፡ የUSAID Transform PHC የደቡብ እና የሲዳማ ክልሎች አስተባባሪ የሆኑት አቶ አገኘው ገብሩ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት፣ የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች አለመኖር ወይም ማነስና የተለያዩ ክፍተቶችን በእነዚህ ህንጻዎች ግንባታ ማሟላትና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ አገልግሎቱን መስጠት የሚያስችል በመሆኑ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ግንባታውን ማከናወኑን አማራጭ ያልነበረው ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል፤ ግንባታው በእናቶችና ሕፃናት ላይ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በጤና ባለሙያው እናቶች ከመውለዳቸው በፊት ሊያገኙ የሚገባውን እንክብካቤ፣ ከወሊድ በኋላ ማግኘት የሚገባቸውን አገልግሎቶች በጥንቃቄ አግኝተው ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ለጤና ባለሙያዎች የክህሎት ማዳበሪያና የተግባር ላይ ልምምድ መስጫ ክፍሎችንም ያካተተ በመሆኑ ይህም ጥራት ያለውን የጤና አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝ በርክብክቡ ላይ ተጠቅሶዋል፡፡ በስተመጨረሻም ለግንባታው በስኬታማነት መጠናቀቅ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላትም ከየዞኖቹ የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡