የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ጥምረት ለጥራት በሚል መረጃን መሰረት ያደረገ የህክምና አገልግሎት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተገለጸ፤

የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መንግስት የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል የአጥቢያ ሆስፒታሎች አራተኛ ዙር መረጃን መሰረት ያደረገ የህክምና አገልግሎት መሰጠት ማስጀመሪያ ፕሮግራም ማካሄዱን አስታወቀ።
የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መንግስት ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የህክምና አገልግሎቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ናፍቆት ብርሀኑ በመክፈቻ ንግግራቸው ትኩረት ያሻቸዋል ብለው ከጠቀሱት አብይ ጉዳዮች መካከል ማህበረሰቡ ፍትሃዊ እና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኝ የተገልጋይ እርካታ ላይ ትኩረት መስጠት፣ የጨቅላ ህጻናት እና የእናቶች አገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻል ሞትን መቀነስ፣ ድንገተኛ እና ጽኑ ህክምና ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ህይወት ለማትረፍ ትኩረት መስጠት እንዲሁም ለተገልጋይ ጽዱ እና ምቹ የጤና ተቋማትን በመፍጠር ረገድ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።
ኃላፊው አያይዘውም በአገራችን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የቀዶ ህክምና ታካሚዎች ስላሉ በህክምና መሳሪያ እጥረት እንዳይጎዱ በትኩረት መስራት ፣ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት ድንገተኛ ሞት እንዳይከሰት ከምን ጊዜም በላይ በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
የደ/ብ/ብ/ህ መንግስት ጤና ቢሮ የህክምና አገልግሎቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቢንያም ሽፈራው ለስራው አጋዥ የሚሆንና ትኩረት የሚሹ የጤና ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሰነድ አቅርበዋል።
በዚህም የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች እንደየ ደረጃቸው የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ከዚህም ውስጥ የሰላም በር የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እና የገረሴ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በ1ኛ ደረጃ ላይ ሲሆኑ፣ ካምባ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሶስተኛ ደረጃ በመውጣት 3ቱም የዴስክ ቶፕ ኮምፕዩተር እና ሰርተፍኬት ተሸልመዋል።
የተቀሩትም ሆስፒታሎች እንደየ አፈጻጸማቸው የሰርተፊኬት ተሸላሚ መሆናቸው ታውቋል።
ከዚህም በኃላ የተሻለ አፈጻጸም እንዲመዘገብ የአጥቢያ ሆስፒታሎችን ለመደገፍ በተቀመጠው ሰነድ የውል ስምምነት ተፈራርመዋል።
በመጨረሻም የአርባምንጭ ተሀድሶ ህክምና ማዕከል ጉብኝት በማድረግ የልምድ ልውውጥ ተደርጓል ።
የደ/ብ/ብ/ህ/ክ መንግስት ጤና ቢሮ