የአርባምንጭ ሪፌራል ሆስፒታል ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ “የሲቲ ስካን ” ማሽን ማስገባቱ ተገለፀ

ቀሪ የሥራ ማስጀመሪያ ቁሳቁሶች ግዥ በጨረታ ሂደት ላይ መሆኑም ተጠቁሟል። በአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ችፍ ክሊኒካል ዳይሬክተር እና የአርባምንጭ ሪፈራል ሆስፒታል ኃላፊ ዶ/ር ደስታ ጋልቻ ከ40 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገዛ የ”ሲቲ ስካን” ማሽን ወደ ሆስፒታሉ መግባቱን ተናግረዋል ። ማሽኑ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው የሚናገሩት ዶ/ር ደስታ በአልትራ ሳውንድ የማይታዩ ጠቅላላ ምርመራዎችን የሚያደርግ በመሆኑ የህብረተሰቡን የዘመናት ጥያቄ የሚመልስ ነው ብለዋል። የማሽኑ መምጣት ዞኑን እና አጎራባች አካባቢዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን ከዚህ ቀደም በማሽኑ አለመኖር በህብረተሰቡ ላይ የሚደርሰው እንግልትና ወጪ የሚያስቀር መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል ። ከ”ሲቲ ስካን” ማሽን በተጨማሪ በ125 ሚሊዮን ብር ዲጂታል ኤክስሬይ ፣ ዘመናዊ አልትራ ሳውንድ ፣ ኤም አር አይ እና ሌሎች የሕክምና አገልግሎት ማስጀመር የሚችሉ ቁሳቁሶች ግዥ ለመፈጸም በጨረታ ሂደት ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት ዶ/ር ደስታ የግዥ ሂደቱ ሲጠናቀቅ ሆስፒታሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል። የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ችፍ ኤክስክዩቲቪ ዳይሬክተር ተወካይ ረዳት ፕሮፌሰር ተክሉ ተሾመ ዩኒቨርስቲው በመማር ማስተማር ፣ ምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎቶችን ዓላማ አድርጎ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል። ሪፈራል ሆስፒታሉ ለማህበረሰቡ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ዘመናዊ የሕክምና ቁሳቁሶች እየተሟሉለት መሆኑንም ተባባሪ ፕሮፌሰር ተክሉ ተናግረዋል ። ተማሪዎችን በተሻለ ሁኔታ ለማስተማር እና ወደ ተለያዩ ሪፌራል ሆስፒታሎች ለሕክምና እና ትምህርት በመላክ የሚወጣውን ሀብት የሚያድን መሆኑን ተወካዩ ገልጸዋል።
የሆስፒታሉ ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሕዝቅኤል አበበ አጠቃላይ የሆስፒታሉ የግንባታ ሂደት 95 በመቶ መጠናቀቁን ተናግረው በውጭ ምንዛሪ ምክንያት የዘገዩ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ አሳንሰሮች እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ለማስገባት በሂደት ላይ ሲሆን በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ ማጠናቀቂያ ሥራዎች እንደቀሩም ተናግረዋል። የቀሩ ሥራዎችን በተያዘው አዲስ ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ለማስገባት በሂደት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
(ጋሞ ዞን መ/ኮሚዩኒኬሽን)፦