የተጠናከረ የጤና ግብዓት አቅርቦት ስርዓት ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ቢሮው አስታውቋል።

ከክልሉ 4 ዞኖች የተመረጡ የጤና ተቋማት የተውጣጡ የግብኣት አቅርቦት ባለሙያዎች በኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት ድርጅት የሀዋሳ ቅርንጫፍን ጎበኝተዋል።

የደ/ብ/ብ/ሕ /ክ መንግስት ጤና ቢሮ ለጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ መጎልበት ቁልፍ የሆነውን የተጠናከረ የጤና ግብኣት አቅርቦት ስርኣት የተጠናከረ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል ።

የደ /ብ/ብ/ሕ /ክ/ መንግስት ጤና ቢሮ ምክትል የቢሮ ሃላፊና የህክምና አገልግሎት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ናፍቆት ብርሃኑ በየደረጃው ያሉ ጤና ተቋማት አስፈላጊ መድሃኒቶችንም ሆነ የህክምና ቁሳቁሶችን አሟልተው በቅርበት የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ከህይወት ጋር የሚገናኘውን መድሃኒት በአግባቡና በበቂ ሁኔታ ማቅረብ ይገባል ያሉት አቶ ናፍቆት ለዚህ ስኬት ተቋማዊ አሰራር መዘርጋት ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል ።

የዘርፉ ባለሙያ የእኔነት ስሜትና ሙያዊ ጥንቃቄ በመድሃኒት አቅርቦት፣አያያዝና ስርጭት እንዲሁም አጠቃቀም ላይ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ምክትል ሃላፊው አስታውቀዋል ።

ለዚህም ዘላቂና የተቀናጀ ተቋማዊ የጤና ግብኣት አቅርቦት ስርኣት መዘርጋቱ ወሳኝ መሆኑን አቶ ናፍቆት ተናግረዋል ።

በቢሮው የመድሃኒትና ህክምና መገልገያ ግብዓቶች አቅርቦት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ፍሊጶስ የተቀናጀ የመድሃኒት አስተዳደር ስርኣት መተግበር ከጀመረ ከ10 አመት በላይ መሆኑን ጠቁመው ለታካሚው ሁሉንም መድሃኒቶች በአንድ ላይ አቀናጅቶ የማቅረብ አሰራር እንደሆነ ጠቁመዋል ።

ያም ሆኖ አልፎ አልፎ ከውጭ የሚገቡ መድሃኒቶች መዘግየትና የዘርፉ ባለሙያ ፍልሰት ክፍተት መፍጠራቸውን ገልጸዋል ።

ከጤና ቢሮው ጋር በመቀናጀት ጉብኝቱን ያዘጋጀው የኢንጀንደርድ ሄልዝ ግብረ ሰናይ ድርጅት አማካሪ አቶ ወንድወሰን መኮንን እንዳሉት ድርጅቱ በደቡብ ክልል በ140 የጤና ተቋማት የግብኣት አቅርቦት ሰንሰለትን ለማጠናከር የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል።

በተለይም ደግሞ የመድሃኒትና የህክምና ቁሳቁሶች አቅርቦት ስርኣት ዘላቂና ተቋማዊ ሆኖ እንዲቀጥል የተቀናጀ ድጋፍና ክትትል በማድረግ፣የአቅም ግንባታ ስልጠና በማዘጋጀትና በዘርፉ ላይ የግምገማና ምክክር መድረኮችን በመፍጠር እገዛ እያደረገ መሆኑን አቶ ወንድወሰን አስታውቀዋል ።

በዚህም ምክንያት ድርጅቱ ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመቀናጀት ድጋፍ በሚያደርግባቸው ተቋማት ያለው የግብኣት አቅርቦት፣ አስተዳደር፣ስርጭትና አጠቃቀም ስርኣት መሻሻል እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

ከእነዚህ ተቋማት የተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ትናንትና ዛሬ በዲላ ሀሮሬሳ ጤና ጣቢያና በኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት ድርጅት የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጉብኝት ማካሄዳቸውን ያነሱት አቶ ወንድወሰን የጉብኝት ፕሮግራሙ የድጋፉ አንዱ አካል እንደሆነም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ መድሃኒት አቅርቦት ድርጅት የሀዋሳ ቅርንጫፍን በካይዘናን ስራ አመራር ስርኣት ትግበራ ስኬታማ በመሆን በቅርቡ በአፍሪካ ካይዘን አዋርድና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ እንደሆነ የቅርንጫፉ ስራ አስኪያጅ አቶ ዘመን ለገሰ ተናግረዋል ።

በፕሮግራሙ ላይ በተቀናጀ የጤና ግብኣት አስተዳደር ስርኣት ትግበራ የተሻለ አፈጻጸም ያሳዩት የዲላ ሀሮሬሳ ጤና ጣቢያ ከጌዴኦ ዞን፣ቶሜ ገሬራ ጤና ጣቢያ ከወላይታ ዞን፣ዶዮ ገና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልና የደዮ ገና ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ከከንባታ ጠንባሮ ዞን እውቅና ተሰጥቷቸዋል ።