የተቀናጀ የዓይን ቆብ ቀዶ ህክምና ባለሙያዎች የምረቃ እና ማስጀመሪያ ፕሮግራም በቡታጅራ ከተማ ተካሔደ

የተቀናጀ የዓይን ቆብ ቀዶ ህክምና ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መንግስት ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ኃላፊ አቶ መና መኩሪያ በመክፈቻ ንግግራቸው ትራኮማ መከላከል ከሚቻላቸው በሽታዎች አንዱ በመሆኑ የአይናችንን ንጽህና ካልጠበቅንና በጊዜ ካልታከምን ለአይን ስውርነት የሚያዳርግና በኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚፈጥር በመሆኑ የህብረተሰባችንን ሕይወት ለመታደግና የበሽታው ስርጭት ምጣኔ እንዳይጨምር ብሎም በሽታውን ከአገራችን ለማስወገድ በቅንጅትና በኃላፊነት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የዘርፍ ኃላፊው አያይዘውም ትራኮማ በሽታን ከዚህ በፊት በትኩረት ተሰርቶበት ውጤት የተመዘገበበት ቢሆንም በጉራጌ፤ ስልጤና ሀዲያ ትኩረት የሚሹ አካባቢዎች በመሆናቸው የስርጭቱ ምጣኔ ሳይጨምር በተመረጡት ዞኖችና ወረዳዎች ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት የሚገባ በመሆኑ የተቀናጀ የዓይን ቆብ ቀዶ ህክምና ባለሙያዎች የአንድ ወር ስልጠና ተሰጥቷቸው የህብረተሰቡን ችግር እንዲቀረፍ አመራሩ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመስጠት ፤የግብአት ጉድለቶችን በማሟላት ከምን ጊዜም ሊሰራበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ወ/ሮ ሕይወት ሰለሞን በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዳሬክተር የትራኮማ በሽታ ትኩረት ተሰጥቶት ያለበት በሽታ ቢሆንም በአንዳንድ ቸልተኝነት ምክንያት በአገራችን አሁንም ከዚህ ችግር ጋር እየተጓዝን በመሆናችን ያላነሰ ቁጥር ያላቸው ወገኖች ድጋፍ የሚሹ በመኖራቸው ይህንን ችግር ለመቅረፍ የሰው ኃይል፤ የግብአት ማሟላት እና ቁርጠኝነት አማራጭ የሌለው በመሆኑ ሁላችንም በትኩረት መስራት ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋሉ፡፡

ዶ/ር አለማየሁ ሲሳይ Orbs International Country Director ትራኮማ የድህነት በሽታ በመሆኑ ታክመው መዳን በሚቻለው በሽታ የሰው ልጅ ታክሞ በማይድነው አይን ስውርነት አደጋ ከመውደቁ በፊት ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንደሚገባ በመግለጽ ከላይ እስከ ታችኛው መዋቅር በትስስር ለማስራት የአመራሩ ቁርጠኝነት ወሳኝ በመሆኑ በጋራ ሰርተን ማስወገድ እንደሚገባ አሳስበዋል፤ በአጠቃላይ ለስራው ትኩረት እንዲኖራው ከተመረጡ የመጡ ዞኖች የመምሪያ ኃላፊዎችና የተመረጡ የወረዳ ጽ/ቤት ኃላፊዎች እንዲሁም የጉራጌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሙሐመድ አህመድ ተሳትፈዋሉ፡፡
ለአሳልጣኝ ዶክተሮች የእውቅና ሰርተፊኬትና የተቀናጀ የዓይን ቆብ ቀዶ ህክምና ለተመራቂ ባለሙያዎች የአንድ ወር ስልጠና እውቅና ሰርተፍኬት በመሰጠት ስልጠናው ተጠናቋል፡፡ የትራኮማ በሽታን በጋራ እንከላከል!

የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መንግስት ጤና ቢሮ