የማህጸን ጫፍ ካንሰር በሽታ መከላከያ ክትባት ጥር 17 ቀን በሀላባ ዞን ቁሊቶ ከተማ መጀመሩን ቢሮው አስታወቀ

በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በዘመቻ የሚሰጠው የማህፀን ጫፍ ካንሰር በሽታ መከላከያ ክትባት በዛሬው እለት በሀላባ ዞን ቁሊቶ ከተማ አልጀበርቲ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት እድሜያቸው 14 ዓመት ለሞላቸው ልጃገረድ ሴት ተማሪዎች እየተሰጠ ሲሆን በዛሬው የመጀመሪያውን ዙር ክትባት 42 ልጃገረድ ሴት ተማሪዎች እንዲሁም ሁለተኛውን ዙር 28 ልጃገረድ ሴት ተማሪዎች መከተባቸውን ከስፍራው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በክትባት መስጫ ስፍራ ክትባት ከሚከተቡ ተማሪዎች አንዳንዶች በሰጡት አስተያየት ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች መረጃ ማግኘታቸው የክትባቱን ጥቅም በማወቅ ያለምንም ማንገራገር ወደ ክትባቱ መምጣት እንዳስቻላቸው የገለጹ ሲሆን አሁንም አንዳንድ የተሳሳቱ መረጃዎች መኖራቸውን በመግለጽ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራውን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመው ማንኛዋም 14 ዓመት የሞላት ልጃገረድ ሴት ይህንን ዕድል በመጠቀም ራስዋን ከመህጸን ጫፍ ካንሰር መከላከል እዳለባት ገልጸዋል።

በሀላባ ዞን ጤና መምሪያ የእናቶች ህጻናትና ስርዓተ ምግብ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ መሀመድኑር ባርጊቾ የማሕጸን ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባቱን ለማሳለጥ ከት/ቤቶችና ከሚዲያ አካላት ጋር በርካታ ተግባራት ማከናወናቸውን ገልጸው ለመምህራን ስልጠና በመስጠት ወደ ክትባት ዘመቻ የተገባ መሆኑን አመላክተው የማይማሩ ሴት ልጃገረዶችን በየቀበሌው በጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች አማካይነት በክትባቱ ተደራሽ እንደሚደረጉ የገለጹት አቶ መሀመድኑር በዞኑ 1,239 ሴት ልጃገረዶች ይከተባሉ ተብሎ እንደሚገመት ገልጸዋል።