የህብረተሰቡን የጤና ሁኔታ ማሻሻል ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ እንደሚቀጥል ተገለፀ

የጤናው ሴክተር ሁለተኛው የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ የህብረተሰቡን ጤና ማሻሻል ሆኖ እንደሚቀጥል የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መንግስት ጤና ቢሮ አስታውቋል

በአፈጻፀም ረገድ የሚስተዋሉ በውስጣዊ እና በውጫዊ ምክንያት የሚጠቀሱ ማነቆዎችን ለይቶ በማውጣት ሁሉም የድርሻውን እንዲወስድና ተጠያቂነትን አማክሎ ተግባርን ማረጋገጥ በዚህም የተግባር ቅንጅት የህብረተሰቡን የጤና ሁኔታ ማሻሻል የመድረኩ ዋነኛ አላማ መሆኑን በደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መንግስት ጤና ቢሮ ኃላፊ በአቶ አቅናው ካውዛ አመላካችነት በሚዛን አማን ከተማ የተጀመረው የጤናው ሴክተር የጋራ የምክክር መድረክ የመጀመሪያ ዙር የጤናው ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም ዋና ዋና ተግባራት ሁለተኛውን የትራስፎርሜሽን ዕቅድ አጀንዳዎችን አቅርቦ እየመከረባቸው ይገኛል፡፡

በዚህም የጤናው ዘርፍ ዋና ዋና ችግሮች ተብለው ከተለዩ ተግዳሮቶች መካከል ፤የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አተገባበር በሚፈለገው ደረጃ አለመሆን ፣በሴክተሩ በሁሉም ደረጃ የማስፈጸም እና የመፈጸም አቅም ውስንነት መኖር፣ የተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ጫና እንዲሁም ተደጋጋሚ የወረርሽኝ ክስተት ከተግዳሮቶች መካከል ተጠቃሽ ከመሆናቸው ባሻገር በጤና ኬላዎች የሚሰጡ አገልግሎቶች በተለያዩ ምክንያቶች የሚጠበቀውን የጥራት እና ሽፋን ደረጃ ያለመድረስ እና ሌሎች ተያያዥ ተግዳሮትን መቅረፍ በሁለተኛውን የትራስፎርሜሽን ዕቅድ አጀንዳዎችን የህብረተሰቡን የጤና ሁኔታ ለማሻሻል አማራጭ የሌለው ተግባር ተደርጎ እንደሚወሰድ ተመላክቷል፡፡

የምክክር መድረኩ በጤናው ሴክተር በየጊዜው ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ለውጥ ለማስመዝገብ የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ ረገድ ጉልህ ፋይዳ ያለው መሆኑን በመገለጽ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ተግባራት ፣የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አተገባበር፣ተከታታይ የባለሙያዎች ስልጠና፣የወረርሽኝ ክስተት እና ተግዳሮቶች ፣የመረጃ አያያዝ ጥራት ውስንነትና ቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ማዕከል ያደረጉ አሳቦች ላይ ውይይት እየተካሄደባቸው ይገኛል ።

የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/ መንግስት ጤና ቢሮ