የሀድያ ዞን ጤና መምሪያ ከሀድያ ዞን ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ መምሪያ ጋር በመተባበር የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ቅድመ መከላከልና መቆጣጠር አፈፃፀምና የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ መድረክ አካሄደ

የሀድያ ዞን ጤና መምሪያ ከሀድያ ዞን ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ መምሪያ ጋር በመተባበር የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ቅድመ መከላከልና መቆጣጠር አፈፃፀምና የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ መድረክ አካሄደ የሀድያ ዞን ጤና መምሪያ ከሀድያ ዞን ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ መምሪያ ጋር በመተባበር የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ቅድመ መከላከልና መቆጣጠር የእስካሁን ሥራ አፈፃፀምና የግንዛቤ ማስጨበጫ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል። በመድረኩም የሀዲያ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ፈለቀ ዶዮሬ፣ የዞኑ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ስምረት ሣሙኤል፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር የሴቶችና ህጻናት እንዲሁም የጤና ጽ/ቤት ኃላፊዎችና የሴት አደረጃጀት አመራሮች ተሳትፈዋል። በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የሀድያ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ፈለቀ ዶዮሬ እንዳሉት የማህጸን ጫፍ ካንሰር በገዳይነቱ ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በርካታ እናቶችን እያጠቃ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በተለይ እድሜያቸው ከ 30 – 49 የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች በየወቅቱ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ የቅድመ ካንሰር ነፃ ምርመራና ህክምና በማድረግ የእናቶችን ሞት መቀነስ እንደሚገባ ገልጸዋል። የሀድያ ዞን ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ስምረት ሣሙኤል በበኩላቸው የማህፀን ጫፍ ካንሰር ወደ ካንሰርነት ከመለወጡ በፊት ቅድመ ምርመራ በማድረግ መዳን የሚቻል በሽታ መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም ነገር ግን ለሴቶች በቂ ግንዛቤ ማስጨበጥና ስልጠና ባለመሰጠቱ በዓመት ከ 7,635 በላይ የሚሆኑ ሴቶች በበሽታው የሚያዙና ከ 4,513 በዚህ በሽታ እንደሚሞቱ ጠቅሰዋል ።
ኃላፊዋ አክለው መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በዞናችን በ 12 ጤና ተቋማት አገልግሎቱን በነፃ እየሰጠ ያለ መሆኑን አስታውሰው አሁን አገልግሎቱን እያገኙ ያሉ ሴቶች ቁጥር ከበሽታው መስፋፋት አንፃር ሲታይ እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ጉዳዮ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በቅንጅት በመስራት ችግሩ ሊቀረፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።