የሀይማኖት ተቋማት የኮቪድ19 ስርጭትን በመከላከልና በማጠናከር ህዝቡን ከአስከፊዉ ቫይረስ ሊጠብቁ እንደሚገባ ተገለፀ

የሀይማኖት ተቋማት የኮቪድ19 ስርጭትን በመከላከል ሂደት የነበራቸዉን ላቅ ያለ ሚና በማጠናከር ህዝቡን ከአስከፊዉ ቫይረስ ሊጠብቁ እንደሚገባ ተገለፀ ፡፡ የሀይማኖት ተቋማት ለማህበረሰቡ ከሚሰጡት መንፈሳዊ ትምህርት ባሻገር አካላዊ ጤንነታቸዉንና ማህበራዊ ደህንነታቸዉን የሚያረጋግጡበትን መንገድ ማሳየት እንደሚገባቸዉና እና በተለይም በአሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ባለዉ የኮቪድ19 ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ላይ ይበልጥ መስራት እንደሚጠበቅባቸዉ የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መ/ ጤና ቢሮ ከክልል፣ከዞንና ከልዩ ወረዳ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በዛሬዉ ዕለት ባደረጉት የዉይይት መድረክ ላይ ተጠቁማል፡፡ በተለያዩ ቤተ–እምነቶች የሚሰጡ ሀይማኖታዊ አስተምሮቶች የራስንና የማህበረሰቡን ጤንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ እንጂ የሚፃረሩ ባለመሆናቸዉ የሀይማኖት ተቋማት የኮቪድ19 ስርጭትን በመከላከል ሂደት የነበራቸዉን ላቅ ያለ ሚና በማጠናከር ህዝቡን ከአስከፊዉ ቫይረስ ሊጠብቁ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ በዉይይት መድረኩ ላይ ቫይረሱ እያሳደረ ያለዉን ቤተሰባዊ፣ ማህበረሰባዊና ሀገራዊ ጫና እንዲሁም የቫይረሱን የስርጭት ሂደት የሚያሳ መረጃ በባለሙያዎች የቀረበ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት እንደ ሀገር 221,544 በቫይረሱ መያዛቸዉን፣ 3,058 ወገኖች መሞታቸዉ እንዲሁም 906 ሰዎች በፅኑ መታመማቸዉን አስታዉሰዉ እንደ ክልልም 6,545 ያህል በቫይረሱ መያዛቸዉ ፣97 ሰዎች መሞታቸዉ እንዲሁም ባለፉት አራት ሳምንታት የመያዝ ምጣኔ 25% መድረሱ እና በፅኑ ለታመሙ ታካሚዎች የሚዉል ሰዉ ሰራሽ የመተንፈሻ አካል አለመኖሩ እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ ቤተ እምነቶች የህዝባቸዉ ደህንነት ከሚያስጠብቁበት ፀሎትና ዱአ ባሻገር በኮቪድ መከላከልና መቆጣጠር ላይ የወጡ መመሪያዎች እንዲከበሩ በማድረግ ሀይማኖታዊና ማህበራዊ ሃላፊነታቸዉን እንዲወጡ ጥሪ ቀርባል፡፡ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም የኮቪድ መከላከያ መንገዶች ማለትም የራስን ንፅህና በአግባቡ ከመጠበቅና አካላዊ ርቀትን ከመጠበቅ ብሎም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ የመጠቀም ልምድን ከማሻሻል ጋር የተያያዙ በመሆናቸዉ ከየትኛዉም ሀይማኖታዊ አስተምህሮ ጋር የሚጋጭ ሀሳብ እንደሌለዉ ከተለያዩ የሀይማኖት ተቋማት የመጡ አባቶች ጠቁመዉ ከዚህ ቀደም ቤተ-እምነቶችን እስከማዘጋት የደረሰዉ ይህ አስከፊ ቫይረስ የባሰ አደጋ ሳያስከትል በቀጣይም አማኞቻቸዉን ከቫይረሱ የመጠበቅ ሃላፊነታቸዉን በተሻለ ለመወጣት በአምልኮ ቦታዎች ሁሉ የኮቪድ መከላከያ መንገዶች ከራሳቸዉ ጀምረዉ በመተግበር ምዕመኑም ተግባራዊ እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል ፡፡