የሀይማኖት ተቋማት የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ስርጭት አሁናዊ ሁኔታን በመረዳት ቫይረሱን በመከላከልና በመቆጣጠር ያላቸው ሚና ትልቅ ነው

የደ\ብ\ብ\ህ\ክ\መ\ ጤና ቢሮ የኤች.አይ.ቪ ስርጭትን ለመቆጣጠርና ለመግታት፣ በተለይም በ2030 አንድም ሰዉ በቫይረሱ እንዳይያዝ የማድረግ ራዕይን እዉን ለማድረግ የሀይማኖት አባቶች ሚና የላቀ መሆኑን ቢሮዉ አስታዉቋል፡፡ የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊና የዘርፈ ብዙ ምላሽ ኤችአይቪ\ኤድስን የመቆጣጠርና የመምራት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በምክክር መድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በአሁኑ ሰዓት የቫይረሱን ስርጭት ካለበት መጠን ለመቀነስና በ2030 አንድም ዜጋ በቫይረሱ እንዳይያዝ የማድረግ ግብን ለማሳካት የሀይማኖት ተቋማት ያላቸዉን ሚና ተናግረዉ በተለይም ቫይረሱ በደማቸዉ የሚገኝባቸዉ ወገኖች የፀረ ኤች.አይ.ቪ መድሀኒታቸዉን በአግባቡ በመዉሰድ በደማቸዉ የተሰራጨዉን የቫይረስ መጠን በተገቢዉ በመቀነስ፣ ጤናማ ኑሮን መምራት እንዲችሉና አምራች ማህበረሰብ ሆነዉ እንዲቀጥሉ የሀይማኖት አባቶች ከሀይማኖታዊ አስተምህሮዉ ጋር የተጣጣመ ትምህርት በመስጠት ሃላፊነታቸዉን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ሃላፊዉ አያዘዉም በክልሉ በደማቸዉ ቫይረሱ ይገኝባቸዋል ተብሎ ከሚገመት ሰዎች ቁጥር አንፃር መድሃኒቱን እየወሰዱ የሚገኙት ሰዎች ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን ገልፀዉ:- ራሳቸዉን በምርመራ አዉቀዉ መድሃኒቱን የሚወስዱ ወገኖችን ቁጥር እንዲጨምርና ስርጭቱን በተፈለገዉ መጠን ለመቀነስ የሀይማኖት አባቶች ጊዜዉን የዋጀ ስራ ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ በምክክር መድረኩ ላይ አለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ፣ ሀገራዊና ክልላዊ የኤች.አይ.ቪ. ስርጭት መረጃ የቀረበ ሲሆን:- በዚህም በሀገራችን 622,326 \ስድስት መቶ ሀያ ሁለት ሺህ ሶስት መቶ ሃያ ስድስት\ ሰዎች ቫይረሱ በደማቸዉ እንደሚገኝና 483,127\ አራት መቶ ሰማንያ ሶስት ሺህ አንድ መቶ ሃያ ሰባት\ ያህሉ መድሃኒት በመዉሰድ ላይ እንደሚገኙ፣ በደቡብ ክልልም 36,775 \ሰላሳ ስድስት ሺህ ሰባት መቶ ሰባ አምስት\ ሰዎች ቫይረሱ ይኖርባቸዋል ተብሎ እንደሚገመትና 26,668 \ ሃያ ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ስልሳ ስምንት\ ያህሉ መድሃኒት እየወሰዱ እንደሆነ ተብራርቷል ። በተጨማሪም አዲስ በቫይረሱ ከሚያዙ ሰዎች ዉስጥ 67 በመቶዉ ከ30 አመት በታች እድሜ ያላቸዉ አፍላ ወጣቶችና ወጣቶች መሆናቸዉ ጉዳዩን አሳሳቢ እንደሚያደርገዉ በመረጃዉ ማየት ተችሏል፡፡ በመድረኩም ‹‹በራስ መተማመን ኤች.አይ.ቪ ፖዘቲቭ ሀገር በቀል ማህበር” አባል ወጣቶች ኤች.አይ.ቪ ከእናት ወደ ልጅ ቢተላለፍባቸዉም መድሃኒታቸዉን በአግባቡ በመጠቀማቸዉና በመንፈስ ጠንካራ በመሆናቸዉ በትምህርታቸዉና በማህበራዊ ህይወታቸዉ ስኬታማ መሆናቸዉን የህይወት ልምዳቸዉን አካፍለዋል፡፡ በመጨረሻም የሀይማኖት አባቶች ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለይቶ በማወቅ እና ከዚህ ጋር ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ በየ ቤተ እምነቶቹ ኤች.አይ.ቪን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ይበልጥ ሊሰሩ እንደሚገባ በዉይይቱ ተመላክቷል፡፡