በአርባምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል የፕላስቲክ እና ሪኮንስትራክቲቭ ቀዶ ሕክምና ዘርፍ ባለሙያ ዶ/ር ደስታ ጋልቻ የከንፈር እና ላንቃ መሰንጠቅ ችግር በተፈጥሮ የሚከሰት ነው ብለዋል። ሰዎች በተለምዶ በባህላዊ እና በሀይማኖት ተፅእኖ የሚከሰት በሽታ ነው የሚሉትን የተሳሳተ አመለካከት በማስወገድ በቀዶ ህክምና ማዳን እንደሚቻል ዶ/ር ደስታ ጋልቻ ገልጸው ህክምናው በአርባምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ከሰኔ 24 ጀምሮ በነፃ እንደሚሰጥ ገልጸዋል ። በአለም ላይ ከሚወለዱ 700 ህፃናት በአንዱ ላይ የከንፈር ወይም የላንቃ መሰንጠቅ ሊከሠት እንደሚችልም ጠቁመው በእርግዝና ወቅት ክትባት ያለማግኘት፣የአልኮል እና አደንዛዥ እፅ፣ የተለያዩ መድሂኒቶች በጽንሱ ላይ በሚፈጥሩት ተጽእኖዎች ሊከሰት እንደሚችል ተገልጿል። ላንቃ ለተሰነጠቀባቸው ታካሚዎች 10 ወር እና ከንፈር ለተሰነጠቀባቸው ከ4-6 ወር የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚሰጥ ሆኖ ታካሚዎች ክብደታቸው 10 ኪ.ግ እና በላይ ሊሆናቸው እንደሚገባም ዶክተሩ ተናግረዋል። ለሕክምና ሲመጡ ህፃናቱ ከተጓዳኝ በሽታዎች ነፃ ሊሆኑም ይገባልም ብለዋል። ህክምናው ስማይል ትሬይን ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር የሚሰጥ ሲሆን የአንድ አስታማሚ የህክምና ቆይታ እና የትራንስፖርት ወጭም በድርጅቱ እንደሚሸፈን ተገልጿል። የታካሚ ቁጥር ታይቶ የጊዜ ገደቡ እንደሚራዘምም ተጠቁሟል በሚል የጋሞ ዞን መንግስት ኮሚዩኒኬሽን መምሪያን ዘገባ የጋሞ ዞን ጤና መምሪያ ፌስቡክ ገጽ ላይ አስፍሯል፡፡