አዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያዎች አፍሪካን የሁለተኛ ዙር ወረርሺኝ ሰለባ እያደረጉ ነው ተባለ

አዲስ የተገኙ የኮሮናቫይረስ ዝርያዎች አፍሪካን ለሁለተኛ ጊዜ በወረርሺኝ ክፉኛ እንድትጠቃ እያደረጉ እንደሆነ የአለም ጤና ድርጅት አስጠነቀቀ፡፡ በአሁን ወቅት በቀላሉ የሚተላለፉት አዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያዎች በመላው አፍሪካ እየተስፋፉ ተጨማሪ ታማሚዎችና ሞት እያስከተሉ እንደሆነ ድርጅቱ ገልጿል፡፡ መጀመሪያ በደቡብ አፍሪካ የተገኘው አዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያ በሌሎች የአፍሪካ አገራት በፍጥነት እየተስፋፋ እንደሆነ በአፍሪካ የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ማትሺዲሶ ሞኤቲ በበይነ መረብ አማካኝነት በተካሄደ ጉባዔ ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ አዲሱ ዝርያ በቦትሰዋና፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ማዮቴ እና በዛምቢያ እንዲሁም ከአፍሪካ ውጪ ባሉ 24 የአለም አገራት መገኘቱ ተረጋግጧል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ በአፍሪካ ኮቪድ 19 ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሲጠቁ 89 ሺህ ገደማ ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን ማጣታቸውን ከሲኤንቢሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡