በ2015 በጀት ዓመት የጤናው ሴክተር የጋራ ውይይት መድረክ ላይ የሴክተሩ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ግመገማ እየተደረገ መሆኑን ጤና ቢሮ አስታወቀ

በ2015 በጀት ዓመት የጤናው ሴክተር የጋራ ውይይት መድረክ ላይ የሴክተሩ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ግመገማ እየተደረገ መሆኑን የደ\ብ\ብ\ህ\ክ\ መንግስት ጤና ቢሮ አስታወቀ በሀዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ የጋራ ውይይት መድረኩ እየተካሄደ መሆኑም ታውቋል፡፡ በጋራ ውይይት መድረኩ የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ ባስተላለፉት መልዕክታቸው ጠንካራ እና የማይበር የጤና ስርዓት በመገንባት የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ የሚከሰቱ የጤና ስጋቶችን የሚመክት ተግበራትን ማከናወን እንደሚገባ አስገንዝበው የጤና እክስቴንሽን ፍኖተ ካርታን በተመለከተ ሁሉን ዓቀፍ የጤና አገልግሎቶችን በማዋሃድ ረገድ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ወደ ውስጥ በተገቢው ፈትሾ ማረም እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የእናቶች ጤና አገልግሎት ከማሻሻል አካያ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል ጉልህ ፋይዳ እንዳለው የተናገሩት ሃላፊው የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ቤደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በጤና ተቋማት የሚሰጠው የጤና አገልግሎት ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ህብረተሰቡንና የባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የክትባት አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ የቅዝቃዜ ሰንሰለቱን የጠበቀና ጥራት ያለው ክትባት በመስጠት የህጻናትን ጤና ማረጋገጥ እንደሚገባ የተናገሩት አቶ እንዳሻው የክትባት አገልግሎት የማይሰጡ የጤና ተቋማት እንዳሉ በማስታወስ ፈጥነው አገልግሎት ሆስፒታሎችን ጨምሮ የክትባት አገልግሎት የሚጀምሩበትን ሁኔታ መፍጠር ይገባል ብለው የስርዓተ ምግብ እጥረት በሽታ ልየታ እና የህክምና አገልግሎት፣ የወባ በሽታን መከላከልና መቆጣጠር፣ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ፣ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል፣ የደም ባንክ አገልግሎቶች ተግባራትን በተሻለ ሁኔታ መምራት፣ የግብዓት ጥራት ቁጥጥር አፈጻጸም፣ የድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ አንጻር ወቅቱን የጠበቀ መረጃን በመለዋወጥ መረጃን ለውሳኔ የመጠቀም ባህልን ማዳበር በእነዚህ ሀሳቦች ላይ ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ በጋራ ውይይት መድረኩ የ2015 በጀት ዓመት መጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም እና የተለያዩ ሰነዶች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። የዞንና የልዩ ወረዳ ጤና መምሪያና ጤና ጽ\ቤት ሃላፊዎች፣ የልማት ዕቅድ አስተባባሪዎች፣ የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊዎች የስብሰባው ተሳታፊዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡