ጂንካ፣ ነሐሴ 03 ቀን ቀን 2014 (ኢዜአ) የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ በደቡብ ኦሞ ዞን ወላጆቻቸውን ላጡ 50 ህፃናት ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚገመት የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ። ቢሮው የትምህርት መርጃ መሳሪያ፣ የደብተር መያዣ ቦርሣ፣ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ እና የኮቪድ-19 መከላከያ ግብአቶችን ነው የደገፈው። “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሀሳብ በጂንካ ከተማ ተገኝተው ድጋፉን ያስረከቡት የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው፤ ሀገራችን አሁን ላይ ያጋጠሟትን ዘርፈ ብዙ ተግዳራቶች እጅ ለእጅ ተያይዘን ልናሻግራት ይገባል ብለዋል። ድጋፉ በተወሰነ ደረጃ የተማሪዎቹን ጫና እንደሚያቃልል ገልጸዋል። በድጋፍ ሥነ ስርዓት ወቅት የተገኙት የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ ለተደረገው ድጋፍ በህፃናቱ ስም አመስግነዋል። የቢሮው አመራሮችና ሰራተኞች ከዞኑ ወጣቶችና አመራሮች ጋር በመሆን የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ያካሄዱ ሲሆን በቀጣይም ለአረጋዊያን የቤት እድሳት ያስጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
Source ENA
የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ