በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ የሃይል ጥቃቶችን ለመከላከልና ለማስቆም ሁሉም ሃላፊነቱን እንዲወጣ ተጠየቀ

በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች መበራከት አሳሳቢ መሆናቸውን ታሳቢ በማድረግ ይህንን ተግባር ለማስቆም የሚደረጉ ጥረቶች ዘላቂ መፍትሄን የሚያመላክቱ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ለዚህም ሁሉም ሃላፊነቱን እንዲወጣ የ/ደ/ብ/ብ/ህ /ክ /መንግስት ጤና ቢሮ የሴቶች ህፃናት እና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት የ2012 ዓ.ም በጀት አመት አፈፃፀምን በመገምገም የ2013 ዓ.ም ዕቅድ ላይ ውይይት ባደረገበት ወቅት መገለፁ ታውቋል።

የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ -19) ወረርሽኝ ለመከላከል ቤት ውስጥ መቆየት ወሳኝ ቢሆንም ይህንን መነሻ በማድረግ በሴቶችና በህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ለተላላፊ በሽታዎች፣ ለስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮችና ለሞት የሚዳርጉ በመሆናቸው ተግባሩን ማስቆም ልዩ ትኩረት ያሻዋል ያሉት የክልሉ ጤና ቢሮ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ወሰን ግዛቸው በቀጣይም ተግባራትን አቀናጅቶ በምራትና በእቅድ በማካተት ውጤታማነቱ በጋራ መረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።ሁሉን አቀፍ የተቀናጀና የአንድ ማዕከል አገልግሎቶችን ማጠናከር የህግ ውሳኔዎችን ለመስጠት የሚያስችሉ የህክምናና ተያያዥ ማስረጃዎችን ከማቅረብ ባሻገር ተጎጂዎች ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ ጥቃቱ የሚያስከትልባቸውን የጤና፣የማህበራዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ ረገድ የሚያበረክተው አስተዋፅዖ የጎላ በመሆኑ ማህከሎችን የማጀራት ተግባራት በሰፊው ሊሰራባቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

በመጨረሻም ከተሳታፊዎች አንዳንዶች በሰጡት አስተያየት በአፈፃፀም ግምገማው እና በምክክር መድረኩ የቀረቡ ሪፖርቶች መነሻነት ሊሻሻሉ እና የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት በተለይም በክስ ወቅት ለሚቀርቡ ቅሬታዎች ፍትሃዊ፣ፈጣንና ተገቢ ምላሽ መስጠት፣ ወጥነት የተከተለ አሰራርን መከተል እንዲሁም በጤና ተቋማት የሚቀርቡ መረጃዎች ተሟልቶ ተገቢ ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለማስቆም በጋራ መረባረብ እንደሚገባ ተናግረዋል ።