ከምግብ እጥረትና አለመመጣጠን ጋር ተያይዘው በህጻናት ጤና ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ህብረተሰቡን በባለቤትነት ማሳተፍ ብሎም የሚዲያ እና የባለድርሻ አካላትን ርብርብ ማጠናከር እንደሚገባ የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መንግስት ጤና ቢሮ ጉዳዩን አስመልክቶ ከሚዲያ አካላት ጋር ባደረገው የውይይት መድረክ አስታውቋል፡፡ የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መንግስት ጤና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት እና ጤና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቀድራላህ አህመድ በንግግራቸው ጤናማና ምርታማ ትውልድን መፍጠር በአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ላይ አወንታዊ ተፅዕኖን መፍጠር ያስችላል በማለት ይህንንም ዕውን ለማድረግ እና ተጠባቂ የሆነውን የባህሪ ለውጥ ተግባራት ማረጋገጥና ማገዝ ለጥቂት ተቋማት ብቻ ተወስኖ የሚተው ባለመሆኑ በተለይም የሚዲያ አካላት የችግሩን አሳሳቢነት በሚመጥን መልኩ የማሳወቅ እና የማስተማር ተግባራትን ማጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል ። ለምግብና ሥርዓተ-ምግብ ዋስትና ችግር መስፍፍት ዝቅተኛ ምርትና ምርታማነት መኖር ፤ ደህንነቱንና ጥራቱን ያልጠበቀ የምርት ሂደት መበራከት፣ ደካማ የቅድመና የድህረ-ምርት አያያዝ ይጠቀሳሉ ተብሏል፡፡
የደብ/ብ/ህ/ክ/መ/ጤና ቢሮ በእናቶችና ህፃናት ጤናና ስርዓተ ምግብ ከፍተኛ ባለሙያ ወ/ሮ መሁባ ሻሚል መቀንጨር ህፃናት አዕምሮአዊና አካላዊ ዕድገት ላይ የሚሳድረውን ጉዳት ለመከላከል እናቶች ከፀነሱበት ጊዜ ጀምሮ ህፃናት ተወልደው ሁለት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ የሚደረግላቸው ልዩ እንክብካቤና ድጋፍ ማተናከር በዚህ ረገድ ግንዛቤ ማስጨበጥ የሚስችሉ ተግባራትን የሚዲያው ሚና ሊጎላ እንደሚገባው አመላክተዋል፡፡