ሙስናንና ብልሹ አሰራርን ከመከላከል አንፃር የተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤት አልተመዘገበባቸውም ተባለ

ሙስናንና ብልሹ አሰራር ከመከላከል አንፃር በኮሚሽኑና በየተቋማት የተሰሩ ስራዎች በተግባር ሲመዘን አመርቂ ዉጤት አለመመዝገቡ የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ መንግስት ጤና ቢሮ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ዳይሬክቶሬት ባዘጋጀው የፊት ለፊት የስልጠና መድረክ ላይ ተገልጿል፡፡ ።

ድንበር ተሸጋሪ እና ዓለም አቀፍ ክስተትና ሰፊ ትስስር ያለዉን ሙስናንና ብልሹ አሰራር ከመለላከል አንፃር በኮሚሽኑና በየተቋማት የተሰሩ ስራዎች በአመለካከትም ሆነ በተግባር ሲመዘን አመርቂ ዉጤት አለማምጣቱ ይነገራል፡፡

ውስብስብ የሆነውን የሙስናንና ብልሹ አሰራር እንደየ ሴክተሩ ባህሪ በተለይም ከቅጥር፣ ከዝውውር ከደረጃ እድገት ፣ከመድሃኒት ስርጭት፣ ከግዢና ንብረት አስተዳደር እንዲሁም ከቁጥጥር ስርአት ጋር በተያያዘ ተጋላጭ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ የሚስተዋሉ ችግሮችን ቀርፎ ለህብረተሰብ የተሳለጠ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላትን ያማከሉ ተግባራት ሊተኮርባቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

የክልሉ ጤና ቢሮ የሥነ- ምግባርና ፀረ ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ኤልሳቤጥ በጋሻው በንግግራቸው ለማህበረሰቡ ፈጣን ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ተቋሙን ከሙስናና ከብልሹ አሰራር መታደግ ይገባል ለዚህም በተግባር የተደገፈ የተቀናጀ ሙስና እስትራቴጂ ማዘጋጀት ፣የህግ ማዕቀፎችን በተግባር ማረጋገጥ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡

ከክልሉ የስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የፊት ለፊት የስልጠና ባለሙያ አቶ ወርቅነህ ተገኔ የተቀናጀ ተቋማዊ የሙስና መከላከል ስትራቴጂ አዘገጃጀት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ፅሁፍ ባቀረቡበት ወቅት የመንግሥት መ/ቤቶች እና የልማት ድርጅቶች ሙስናን የመከላከል ተግባርን በባለቤትነት ማከናወን እንዳለባቸዉ ተናግረዋል፡፡

በስልጠናው ላይ ከክልሉ ጤና ቢሮ ማኔጅመንት አባላትና ሰራተኞች ከፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ መሆናቸው ተመልክቷል፡