በጤናው ሴክተር ወቅቱ የሚጠይቀውን ድርብርብ ሃላፊነት በብቃት ለመወጣት የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ማጎልበት…

በጤናው ሴክተር ወቅቱ የሚጠይቀውን ድርብርብ ሃላፊነት በብቃት ለመወጣት የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ማጎልበት ፤ በተስተዋሉ ውስንነቶች አፅንዖት ሰጥቶ ተግባርን ማስቀጠል እንደሚገባ የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መንግስት ጤና ቢሮ የ2012 በጀት አመት የጤና ልማት አጋር ድርጅቶች ግብረ ኃይል አፈጻጸም ግምገማ በጋራ እየገመገመ ባለበት ወቅት መገለፁ ታውቋል፡፡

የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መንግስት ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አቅናው ካውዛ በመልዕክታቸው በጤናው ሴክተር የተቀመጡ የትራንስፎርሜሽን አጀንዳ የግብ ስኬቶችን ማረጋገጥ ዋና የትኩረት አቅጣጫ በማድረግ ወደ ተግባር መገባቱ የሚታወስ መሆኑን በማንሳት ከተመዘገቡ አበረታች ውጤቶች ባሻገር ተጨባጭ ለውጥ ያሰፈልጋቸዋል፤ ያሏቸውንም ተግባራት ሃላፊው በንግግራቸው አመላክተዋል።

ኃላፊው አክለውም ፍትሃዊ የጤና አገልግሎትን ማዳረስ ፣ መረጃን ለውሳኔ የመጠቀም ባህልን በተገቢው ማሳደግ ፣ እንዲሁም በአፈፃፀም ደረጃ የተስተዋሉ ጉድለቶችን ማረም ፣ የእናቶችና ህፃናት ጤናን አገልግሎት ማሻሻል ተግባራት ትኩረት እንደሚሹ በሰፊው አስገንዝበዋል ፡፡ ወቅታዊ ወረረሽኝ በሆነው የኮሮና ቫይረስ መከላከልና መቆጣጠር ተግባራት በዚህም ሳቢያ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ችግሮችን መቀነስ በድርብ ሃላፊነት የሚፈፀም ተግባር መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የጤና ልማት አጋር ድርጅቶች ግብረ ሃይል ዋና ሰብሳቢ አቶ አገኘው ገብሩ በባለድርሻ አካላቱ የተከናወኑ ተግባራትን፣ ያጋጠሙ ችግሮች እና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎችን እንዲሁም በቀጣይ መሻሻል ያለባቸውን ተግባራት አመልክተዋል ፤በመሆኑም የመንግስትን አቅጣጫና ፖሊሲ ተከትለው የጤና ተግባራትን የሚደግፉ ባለድርሻ አካላት በኮሮና ቫይረስ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት የተስተዋለው አርሃያነት ያለው የመደጋገፍ ፣ በሌሎች የመደበኛ የጤና አገልግሎቶችም ሊደገም እንደሚገባው ፤ተቀናጅቶ ተግባርን መፈፀም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ተግባር መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

በዚሁ ጊዜ ከተሳታፊዎች አንዳንዶች በሰጡት አስተያየት የኮሮና ቫይረስን በመከላከልና በመቆጣጠር ከሚከናወኑ ተግባራት ባሻገር መደበኛ የጤና አገልግሎቱ ያለበትን ደረጃ በጋራ ለመገምገም ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሚከናወን የምክክር መድረክ በመሆኑ ከሌሎች ጊዜያቶች በድርብ ድርብርብ ሃላፊነት የሚካሄድ በመሆኑ የሚቀመጡ የትኩረት አቅጣጫዎች ይህንኑ በሚያመላክት መልኩ ተደራሽ መደረግ እንደሚገባቸው በማስገንዘብ፦ የጤና አገልግሎት ጥራት ዘላቂነት ለማገዝ አጋር ድርጅቶች ሚና የላቀ መሆኑን ባያጠያይቅም በቀጣይ የመንግስት አቅምን በአጠናክሮ መሄድ ወቅቱ የሚጠየቀው ጉዳይ መሆኑን መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በመጨረሻም በጋራ የምክክር መድረኩ የክልሉ ጤና ቢሮ የማኔጅመንት አባላት ፣የዞን ጤና መምሪያ ሃላፊዎች እና ልዩ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ሃላፊዎች ፣የጤናው ሴክተር የልማት አጋር ድርጅቶች የሥራ ሃላፊዎች /ተወካዮች/፣ እንዲሁም ባለሙያዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በጉባሄው ተሳታፊ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡