ህብረተሰቡ የሚያጋጥመውን የጤና ችግሮች ለማቃለል የጤና መሠረተ-ልማት መስፋፋት ጉልህ አስተዋጽዖ አለው

ህብረተሰቡ የሚያጋጥመውን የጤና ችግሮች ለማቃለል የጤና መሠረተ-ልማት መስፋፋት ጉልህ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት ተገለፀ

ህብረተሰቡ የሚያጋጥሙትን የጤና ችግሮች ለማቃለል የጤና መሠረተ-ልማት ተደራሽነት ማጠናከር ጉልህ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/ መንግስት ጤና ቢሮ በከፋ ዞን በዴቻ ወረዳ ለሚገነባው ስራ ህይወት ጤና ጣቢያ ስራ ለማስጀመር የሚስችል የውል ስምምነት በተፈራረመበት ወቅት መገለፁ ታውቋል፡፡

ስራ ህይወት ጤና ጣቢያ ግንባታ ወጪው በክልሉ መንግስትና በጎጎታ ኬር የከምባታ ጠምባሮ ዞን ህዝቦች ልማት ማሕበር የሚሸፈን መሆኑ ታውቋል፡፡

በውል ስምምነቱ ላይ የተገኙት የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/ መንግስት ጤና ቢሮ ምክትል የቢሮ ሃላፊና የፕሮግራም ዘርፍ አስተባባሪ አቶ መና መኩሪያ የጤና ጣቢያው ግንባታ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋፋት የእናቶችና ህፃናትን ጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት ማሻሻልን ጨምሮ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስርጭትን ለመግታት ከሚያበረከረተው አስተዋፅዖ ባሻገር እርስ በርስ መተባበር ባህልን በማጎልበት ለግለሰቦች ፣ለሌሎችም መሰል ማህበራት መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማት፣ በአርአያነቱ ተጠቃሽ ሊሆን የሚችል ተግባር መሆኑን በማውሳት ለማህበሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የጎጎታ ኬር የከምባታጠምባሮ ዞን ህዝቦች ልማት ማሕበር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አብነት ወትሮ በበኩላቸው የልማት ማህበሩ ዋናኛ አላማ መልካም ተግባራት ክፍያቸው መልካም ነው መርህን አንግቦ ስፍራና አከባቢ ሳይወስነው ማህበሩ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ ለሚከሰቱ ችግሮች ሰብአዊ ድጋፍ ከማድረግ ጀምሮ ህብረተሰቡን በዘላቂነት በሚያሥተሳስሩ ፕሮጀክቶች ላይ በስፋት ተሳታፊ እንደሚሆን በማንሳት በከፋ ዞን በዴቻ ወረዳ የሚገነባው ስራ ህይወት ጤና ጣቢያ የዚሁ ተግባር ማሳያ በመሆን የህብረተሰቡን ዘላቂ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው በማለት የጤና ጣቢያው ግንባታ ጥራትና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጤና ጣቢያውን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እና የሚፈለገውን ጥራት ጠብቆ ለማጠናቀቅ ስድስት ወር እንደሚፈጅ ተገልጿል፡፡